Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በደቡብ ክልል ለሥራ ዕድል ፈጠራ የተሰራጨ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ አልተመለሰም

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ የተሰራጨ ብድር አለመመለሱ ተገለጸ፡፡
የደቡብ ክልል የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ቡልቻ እንደገለጹት÷ 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በብድር ለወጣቶች ሥራ ዕድል የተሰራጨ ገንዘብ አልተመለሰም።
የብድር ስርጭቱ ችግር ያለበት መሆኑ፣ ብድሩን በዘመቻ፣ ቶሎ ለማዳረስ ተብሎ ለወጣቱ በቂ ግንዛቤ ባልተፈጠረበት እንዲሁም የአዋጭነት ጥናት ሳይደረግ መሰራጨቱ እና ዋስትና አለመኖሩ ለብድሩ አለመመለስ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የታችኛው መዋቅር አመራር፣ ባለሙያና አሰራጩ አካል ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ የተሰራጨን ብድር የመጠየቅ ክፍተት ዕዳው እንዳይመለስ አድርጎታልም ነው የተባለው፡፡
ሥራ አጥነት ጎልቶ የሚታየው በከተሞች ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ÷ ሥራ ፈላጊዎችን በመለየት፣ በማደራጀት፣ ጊዜያዊ እና ቋሚ ሥራ በመፍጠር፣ በሥራ ፈላጊዎች መነሳሳትና በመንግስት ድጋፍ ሥራ እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በደቡብ ክልል ካለው ሕዝብ የከተማ ሥራ አጥ ምጣኔ 18 ነጥብ 1 በመቶ መሆኑን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ መረጃ እንደሚያመለክት የተናገሩት አቶ ማርቆስ÷ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አስር ዓመታት 2 ሚሊየን 398 ሺህ ዜጎችን ሥራ ለማስያዝ ታቅዷል ብለዋል።
ለወጣቶች ሥራ አለመፍጠር ቤተሰብ፣ አካባቢን እና ሀገርን እንደሚጎዳ የተናገሩት ዳይሬክተሩ የሥራ ፈላጊው መንግስት ሁሉን ነገር እንዲያመቻችለት መፈለግ፣ በመንግስት ያሉ የመሬት፣ የብድር እና ስልጠና ያለመመቻቸት ችግሮች መሆናቸውን አንስተዋል ሲል የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version