Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ክብረ ንጽህና ተይዞ ዓረብ ሀገር መሄድ አይቻልም ብሎ በማታለል ታዳጊዎችን የደፈረው ግለሰብ ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2013 (ኤፍ ቢሲ) ክብረ ንጽህናችሁን ይዛችሁ ዓረብ ሀገር መሄድ አይፈቀድም በማለት ሁለት ታዳጊዎችን በማታለልና በማስፈራራት የደፈረው ግለሰብ በ20 ዓመት እስራትና በገንዘብ መቀጣቱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ወንጀሉን የተባበረችው ባለቤቱም በ10 ዓመት እስራትና በገንዘብ መቀጣቷ ነው የተገለጸው፡፡
የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ራዲያ ቱራ ÷ግለሰቡ “ታዳጊዎች ልጃገረድ ሆነው ዓረብ ሀገር መሄድ አይፈቀድላቸውም” በማለት አታሎና አስፈራርቶ መድፈሩን ገልጸዋል።
ተከሳሽ ሙስጠፋ ከድር ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ሚግራ መናኸሪያ አካባቢ በሚገኝ ሰላም መኝታ ቤት አልጋ ይዞላቸው ምሽት አራት ሰዓት ላይ ታዳጊዎቹን መድፈሩን ዋና ኢንስፔክተሯ ተናግረዋል።
የታዳጊዎቹ ዕድሜ 14 እና 15 ዓመት መሆኑን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተር ራዲያ ÷ ከአርሲ ዞን ዲገሉና ጥዮ ወረዳ ከቤተሰቦቻቸው ጠፍተው በአሰላ ከተማ መገኘታቸውን ገልፀዋል።
የተከሳሽ ባለቤት ሰዓዳ ወይንም በቅፅል ስሟ ቢፍቱ ሙሐመድ ግንቦት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ታዳጊዎችን ዓረብ ሀገር እልካቸዋለሁ በማለት ከአሰላ ወደ አዳማ እንዳመጣቻቸው ዋና ኢንስፔክተር ራዲያ አመልክተዋል።
በማግስቱ ግለሰቡ ለራሱና ለባለቤቱ አንድ መኝታ እንዲሁም ለሁለቱ ታዳጊ ሴቶች አንድ መኝታ ቤት በመከራየት ምሽት አራት ሰዓት በጩቤ አስፈራርቶ መድፈሩን በሰውና በሰነድ ማስረጃ መረጋገጡን ተናግረዋል።
የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ባዋለው ችሎት 1ኛተከሳሽ ሙስጠፋ ከድር በ20 ዓመት እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ መወሰኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ 2ኛ ተከሳሽና የወንጀሉ ተባባሪ የሆነችው ባለቤቱ ሰዓዳ ሙሐመድ በ10 ዓመት እስራትና በገንዘብ እንድተቀጣ ውሳኔ መስጠቱን ዋና ኢንስፔርተር ራዲያ ቱራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version