የሀገር ውስጥ ዜና

አሸባሪው ህወሓት ተከታዮቹንና የታጠቀውን መሳሪያ ጥሎ እየፈረጠጠ ነው

By Meseret Awoke

August 25, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት ተከታዮቹንና የታጠቀውን መሳሪያ ጥሎ እየፈረጠጠ ሽንፈቱን እየተከናነበ መሆኑን በወሎ ግንባር የሚገኙ የጦር አዛዦች ተናገሩ።

ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች ድል እየተደረገ ተከታዮቹ እየተደመሰሱና እየተማረኩ ይገኛሉ።

በወሎ ግንባር የ21ኛ ጉና ክፍለጦር አዛዥ ኮሎኔል ተክሉ ሁሪሳ የተናጠል ተኩስ አቁሙን ተከትሎ የሽብር ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች ዝርፊያ፣ ንፁሃንን የመግደልና የውንብድና ተግባራት መፈፀሙን አስረድተዋል።

አሸባሪው ትህነግን ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከክልል ልዩ ሀይሎችና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር በተካሄዱ ወታደራዊ እርምጃዎች ጠላትን በመደምሰስ ቁልፍ ቦታዎችን መቆጣጠር ተችሏል ነው ያሉት።

የ11ኛ ክፍለጦር አዛዥ ኮሎኔል መኳንንት በበኩላቸው÷ አሸባሪው ህወሓት የወገን ጦርን ፈፅሞ የማይቋቋመው መንኮታኮት እንደገጠመው ተናግረዋል።

ምላሱ የማይሞተው ትህነግ ያልያዛቸውን አካባቢዎች እንደተቆጣጠረ፣ ያልማረከውን እንደማረከ የሀሰት ፕሮፖጋንዳውን በመንዛት ላይ መሆኑን የተናገሩት ኮሎኔል መኳንንት÷ በሀሰት ፕሮፖጋንዳው የተደለሉ ጀሌዎቹ የወረሯቸው አካባቢዎች መቃብራቸው መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

አሸባሪው ቡድን ደመሰስኳቸው ባላቸው የ21ኛ ጉና እና 11 ክፍለጦሮች ድባቅ እየተመታ ይገኛል ነው ያሉት።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በወሎ ግንባር አውደውጊያዎች ተገኝቶ የጀግና የቁርጥ ቀን ልጆችን ድል አረጋግጧል።

የ112ኛና 210ኛ ኮሮች አዛዢ ብርጋዴር ጀኔራል ዓለሙ አየነው ጠላትን በአጭር ጊዜ ለመደምሰስ የተቀናጀ ዘመቻ እየተተገበረ ሲሆን፥ ፍሬ በማፍራት ጁንታው ሽንፈት እንደተከናነበና በተስፋ መቁረጥ ወደ ተራ ዝርፊያ መውረዱን ተናግረዋል።

በርካታ ተከታዮቹ የተደመሰሱበት ቡድኑንና መሪዎችን የማደን ተግባርም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

ነፃ በወጡ አካባቢዎች ርዝራዦችን የመልቀምና የማፅዳት ተግባር በመከወን ላይ ሲሆን÷ የህዝቡ ትብብር ድሉን አቅርቦታል ብለዋል።

በአፈወርቅ እያዩ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!