አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንዳሉት ኢትዮጵያ በታሪኳ ሉአላዊነትን በማረጋገጥ የህዝብ አንድነትን በማስጠበቅ የራሷን፣ የቀጠናውንና የአፍሪካን ሰላም እና ደህንነት በማስጠበቅ ከትውልድ ትውልድ በማስተላለፍ የጥቁሮች ኩራት መሆኗ የማይፋቅ ታሪክ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
“ሃገራችን በርካታ ጠላቶች ቢኖሯትም ሁለቱ ዋና ዋና ጠላቶች ግን ድህነትና በድህነት ውስጥ በእጅ አዙር በውስጥና በውጪ የሚመሩት ችግሮች ናቸው” ብለዋል።
ድህነትን ለማሸነፍ ዜጎች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በድህነት ውስጥ በእጅ አዙር በውስጥና በውጪ የሚመሩ ችግሮችን ለመፍታት ግን የተለየ እውቀት፣ ክህሎት፣ ጥበብ እና በአንድነት ላይ የተመሰረተ ትብብር ያስፈላጋል ብለዋል።
በመሆኑም የምሁራን ሚና ወሣኝ በመሆኑ መድረኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
አያይዘውም ምሁራን በህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በዲጅታል ዲፕሎማሲ እና በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እና ሌሎችም ማህበረሰቡን ከማንቃት አንጻር የሰሩትን ስራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ በዶክተር ዲማ ነገዎ፣ ዶክተር ካይሬዲን ተዘራ እና ዶክተር አየነው ብርሃኑ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በውይይቱ ላይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን ተሳታፊዎች ናቸው።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!