የሀገር ውስጥ ዜና

ለአሸባሪው ህወሓት ሲሰሩ በነበሩ የሰራዊት አባላት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጠ

By Meseret Awoke

August 25, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ዕዝ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የዕዙ የሰራዊት አባላት ሆነው ለአሸባሪው ህወሓት ሲሰሩ በነበሩ የሰራዊት አባላት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የሰራዊት አባላቱ ለህገ-መንግስቱና ለሃገራቸው የገቡትን ቃል ኪዳን ወደጎን በመተው የሰራዊቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች አደጋ ላይ የሚጥሉና የትግራይ ልዩ ሃይልን የሚያጠናክሩ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸው በችሎቱ ተነስቷል፡፡

በተለይም የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ምስጢራዊ ሰነዶች ለትግራይ ልዩ ሃይል አሳልፈው በመስጠት፣ የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ትጥቆች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ ምስጢራዊ ቡድን በማደራጀትና መሳሪያዎቹን በማበላሸት ስራ ላይ ተጠምደው እንደነበር በችሎቱ ተገልጿል፡፡

በዚህ የተከሳሾች መዝገብ ስር፡-

1. ለግዳጅ የተዘጋጁ መሳሪያዎች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ፣

2. ሰራዊቱ ሽብርተኛውን የሸኔ አባላትን ለመደምሰስ በሚንቀሳቀስበት ዕለት ቀድሞ መረጃ በመስጠትና ተልዕኮው ተፈላጊውን ውጤት እንዳያገኝ በማድረግ፣

3. የሰራዊቱን ምስጢራዊ ክንዋኔዎች ለሽብርተኛው አካል እንዲደርስ በማድረግ፣

4. በበላይ አካል የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ወደጎን በመተው ከሽብርተኛው አካል የሚሰጣቸውን ድብቅ አጀንዳ መፈፀም በሚያስችላቸው አካሄድ ላይ ብቻ ማተኮር፣

5. የትግራይ ልዩ ሃይሎች “የብልፅግና ወታደሮችን” ድል እያደረጉ ነው የሚል ሽብር በመንዛት በሰራዊቱ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ የሰራዊት አባላትን በማነሳሳት የቆሙለትን አላማ ወደጎን በመተው የወንጀል ድርጊታቸው አካል እንዲሆኑ በማድረግ፣

6. ከቆሙለት ሃገራዊ አላማ ይልቅ ለክልል ልዩ ሃይል የሚጠቅሙ ተግባራትን ማከናወን የሚሉ ክሶች ተዘርዝረዋል።

ተከሳሽ የሰራዊት አባላትም የቀረቡላቸውን ክሶች ክደው የተከራከሩ ሲሆን የዕዙ ፍትህ ቡድን የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርቦ መከራከሩን የዘገበው ኢቢሲ ነው፡፡

የተከሳሾች ጠበቃ በበኩሉ ተከሳሽ የሰራዊት አባላቱ ከዚህ ቀደም ሃገራቸውንና ህዝባችውን ለማገልገል በርካታ አወንታዊ ተግባራትን ያከናወኑ መሆናቸውንና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍርድ ቤቱ የቅጣት ማቅለያ እንዲያደርግላቸው ጠይቋል፡፡

ግራ ቀኙን ያዳመጠው ወታደራዊ ፍርድ ቤትም ተከሳሾቹ በቀረቡባቸው ክሶች ላይ በትክክል መከላከል ያልቻሉ በመሆኑ ጥፋተኛ ናቸው ሲል በመወሰን የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱን ማጠናቀቁን የደቡብ ዕዝ ኢንዶክትሪኔሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!