የሀገር ውስጥ ዜና

በደብረ ብርሃን ከ1 ሺህ 500 በላይ ግለሰቦች በሕገ-ወጥ መንገድ ተደራጅተው ተገኙ

By Alemayehu Geremew

August 25, 2021

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደብረብርሃን ከተማ በተለምዶ 633ቱ የቤት ሕብረት ስራ ማሕበራት በሚል ከተደራጁና ዕውቅና ከተሰጣቸው ማህበራት ውስጥ ከ 1 ሺህ 500 በላይ ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ ተደራጅተው መገኘታቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ ከከተማና ከቀበሌ አመራሮች ጋር በማህበራቱ ጉዳይ መክረዋል።

633ቱ ማህበራት ሲደራጁ 73 የተለያዩ ቦታዎቸ ክፍት የነበሩ ቢሆንም በ65ቱ ክፍት ቦታዎች 1 ሺህ 408 ሰዎች በህገወጥ መንገድ በመደራጀታቸው የከተማው ከንቲባ ኮሚቴ ማህበራቱ ሙሉ በሙሉ እዲሰረዙ መወሰኑ ተገልጿል።

በቀሪ 560 ማህበራት ውስጥም 110 ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ ተደራጅተው ተገኝተዋል ያሉት ከንቲባው እነዚህ ግለሰቦች ማሕበራቱ ሳይፈርሱ ግለሰቦችን ብቻ እንዲወጡ መወሰኑን አስረድተዋል።

አሁንም መረጃ የማጣራት ስራው ቀጣይነት እዳለው የገለፁት ከንቲባው በዚህ ህገወጥ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በህግ ለመጠየቅ ይሰራል ብለዋል።

አበበ የሸዋልዑል