አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይድ) ኢትዮጵያ እያካሄደች ላለው የበረሃ አንበጣ መከላከል ስራ የ800 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት (ፋኦ) በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ በተመለከተ ባዘጋጀው የውይይትና ድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ድርጅቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተወካዮች እንዲሁም የዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተወካዮች ተገኝተዋል።
ወቅታዊ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝን በተመለከተ ውይይት መደረጉን በጣሊያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የበረሃ አንበጣ ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች ከ485 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአስቸኳይ ለመከላከል እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
የበረሃ አንበጣ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ የሀብት ማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑም ነው የተገለጸው።
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትም ኢትዮጵያ እያካሄደች ላለው የበረሃ አንበጣ መከላከል ስራ የ800 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ በመድረኩ ላይ አስታውቋል።
በሮም የኢፌዴሪ ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ዘነቡ ታደሰ የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት እና ሌሎች አጋር አካላት የበረሀ አንበጣ ስርጭትን ለመግታት ለኢትዮጵያ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አምባሳደር ዘነቡ በአሁኑ ሰአት በድጋሚ የተከሰተው የበረሀ አንበጣ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፥ የሎጅስቲክስ፣ አቅም ግንባታ፣ መድሀኒትና መሳሪያዎች እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።