የሀገር ውስጥ ዜና

በተያዘው በጀት ዓመት 25 የገጠር ከተሞችና መንደሮችን በፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ተባለ

By Meseret Demissu

August 24, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2014 በጀት አመት 25 የገጠር ከተሞችና መንደሮችን በፀሃይ ኃይል ማመንጫ አማካኝነት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ  ገልጿል።

ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በደቡብ እና በሶማሌ ክልሎች ባሉ በተመረጡ የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች በ6 ሎቶ ተከፍሎ ይከናወናል ሲሉ  የብርሃን ለሁሉ ፕሮጀክት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሁሉንአየሁ ደጀኔ ተናግረዋል፡፡

አጠቃላይ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ  8 ሺህ ኪሎ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ይሆናል ያሉት ኃላፊው፥ 145 ሺህ 169 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በዚህም 68 ነጥብ 7 ኪ.ሜ የመካከለኛና 233 ነጥብ 3 ኪ.ሜ የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ ይከናወናል ሲሉ ኃላፊው ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡

የአየር ንብረት ሁኔታ ደመና በሚሆንበት ወቅት እያንዳንዱ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ በውስጡ ሶላር ፓናል፣ ዲዝል ጄኔሬተር እና ባትሪ ያሉት በመሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይቋረጥ ያግዛሉ ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 20 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ብድር እና 161 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር በጀት ተይዞ ስራውን ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

አቶ ሁሉንአየሁ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ሴቶችንና ህጻናት በምግብ ማብሰልና መሰል ስራዎች ላይ የሚያጠፉትን አላስፈላጊ ጊዜ በሌሎች ውጤታማ የስራ አንቅስቃሴዎች ላይ እንዲያውሉ ከማስቻል ባሻገር ለትምህርት፣ ለጤና፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒዩኬሽን፣ ለእርሻ አገልግሎት ትልቅ ጠቄሜታ ያመጣል ሲሉ  መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!