አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕልውና እና ሉዓላዊነትን ለማስከበር የገባንበት ጦርነት ፍጻሜው የሚወሰነው በሕልውናችን እና በሉዓላዊነታችን ላይ አደጋ ሆኖ የተጋረጠው የአሸባሪው የትህነግ ቡድን ከአማራ ክልልም ሆነ ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ተደምስሶ ሲጠፋ ብቻ መሆኑን የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡
የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ ሽብርተኛ ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ ጠራርጎ ለማስወገድ እየተደረገ ባለው ጦርነት አሸናፊነታችን የሚመዘነው አነስተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ መሥዋዕትነት በመክፈል አሸባሪው የትህነግ ቡድን ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድቀት በማድረስ ቡድኑን ለዘላለሙ እንዳያንሰራራ በማድረግ እና ባለማድረግ ብቃታችን ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ አንጻር ባለፉት ቀናት ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ እና ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች እና እንዲሁም ሀቀኛ ፋኖዎች እና በየአውደ ውጊያው አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችና ወጣቶች በአሸባሪው የትህነግ ታጣቂዎች ላይ እያደረሱት ያለው የሰብአዊ እና ቁ0ሳዊ ውድመት ሲታይ በጠላት ላይ ድል እየተቀዳጀን መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላልም ነው ያሉት፡፡
አሸባሪው ትህነግ ወረራ በፈጸመባቸው በማይጠብሪ፣ በጋይንት፣ በጋሸና፣ በመርሳ፣ በወልድያ፣ በደብረ ዘቢጥ እና አካባቢዎች የጠላት ኃይሎች ላይ ጀግኖቻችን በወሰዱት የማጥቃት ዘመቻ በእያንዳንዷ ቀን እንደ የጠላት ኃይል ተገቢውን ቅጣት እየተሰጣቸው እንደቅጠል እየረገፉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
“የጠላት ኃይልም ከገባበት የአማራ መሬት እንዳይወጣ ተደርጎ በወዳጅ የጦር ኃይል እየተወገረ ይገኛል” ብለዋል በመግለጫቸው።
አያይዘውም “ከትህነግ መሰሪ ክፋት አኳያ አሁን እየወሰድንበት የሚገኘውን የማያዳግም እርምጃ አጠናክረን ከማስቀጠል በስተቀር በድል አድራጊነት ስሜት ልንቀዛቀዝ አይገባምም” ነው ያሉት፡፡
የተጀመረው ትግልም አላማው እስከሚሳካ የበለጠ እየጋለ የሚሄድ እንጅ የታሰበው ግብ ተሳክቶ የጋራ ድልን በጋራ እስከሚበሰር በምንም ምክንያት ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ የሚሄድ እንዳልሆነም አብራርተዋል።
ጠላት ላይ እየተደረገ ያለው የህልውና፣ የፍትህና የነፃነት ዘመቻ የማጥቃት ማርሹን እየጨመረ በፍጥነት መጓዝ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
ይህ እንዲሆን ሁሉም በተሰማራበትና በተሰጠው ተልዕኮ ላይ ትኩረት በማድረግ መወጣት እንደሚገባው ጠቅሰው፥ ለአፍታም ቢሆን በምንም ምክንያት ለጋራ ጠላት መዘናጋትና መለሳለስ እንደማይገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሽብርተኛው ቡድን በገባባቸው የአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ በንጹሃን ዜጎች ላይ ከአዕምሮ በላይ የሆኑ ግፎች መፈጸሙን በመጥቀስም፥ የንጹሃን ደም አልበቃ ብሎት የደሃ አርሶ አደሮችን የጋማ እና የቀንድ ከብቶችን ጭምር የሚበላውን በልቶ፣ ጭኖ የሚወስደውን ወስዶ ያልቻለውን ደግሞ በጥይት ደብድቦ መግደሉንም አስታውቀዋል።
“ከዚህ ባለፈም በከተሞች በማኅበራዊ ተቋማት፣ በግለሰቦችና የመንግስት ንብረት ላይ የፈጸመው ውድመት መጠን ቡድኑን በቁሙ ከመቅበር በስተቀር የሚመጥነው የቅጣት እርምጃ ይኖራል ብሎ ለመገመት ያዳግታል” ብለዋል፤ ለዚህ ቡድን የሚራራ አማራና ኢትዮጵያዊ መኖር እንደሌለበት በመጥቀስ።
የሚዲያ ተቋማት አሸባሪው የትህነግ ቡድን የፈፀማቸውን ሁለንተናዊ ኃጢአቶች በመሰነድ እውነታውን ለዓለም ማሳወቅ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አውስተዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!