የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ መካከል በትምህርት ዘርፍ ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

By Tibebu Kebede

January 31, 2020

አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያና በደቡብ ኮሪያ መካከል በትምህርት ዘርፍ ያለው የትብብር ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።

በደቡብ ኮሪያ ትምህርት ሚኒስትር የዓለም አቀፍ ትምህርት ብሔራዊ ኢንስቲቲዩት ምክትል ዳይሬክተር የተመራ ልዑክ ከኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱም በደቡብ ኮሪያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የትምህርት ዘርፍ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

በደቡብ ኮሪያ ትምህርት ሚኒስትር የዓለም አቀፍ ትምህርት ብሔራዊ ኢንስቲቲዩት ምክትል ዳይሬክተር ካንግ ኪዩንግ ሱግ ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ባላት የረጅም ጊዜ ግንኙነት በልዩ ልዩ መስኮች ድጋፍና ትብብር ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።

በተለይም በትምህርትና ስልጠና መስክ የምታደርገውን ድጋፍና ትብብር በማጠናከር የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በሚጠይቀው የትምህርትና ስልጠና መስክ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ በበኩላቸው፥ የትምህርት ፍኖተ ካርታን ጨምሮ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የትምህርትና ስልጠና ማሻሻያ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢንስቲቲዩቱ በትምህርት ዘርፍ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ በመሆኑ ምስጋና ያቀረቡት ሚኒስትር ዲኤታዋ፥ ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።