አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከሶማሊያ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አዲዋ የሱፍ ራጌ በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።
በውይይታቸው ሶማሊያ ወደፊት በወታደራዊ መስክ ራሷን ችላ ለመቆም በምታደርገው ጥረት ዙሪያ መምከራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሀኑ ጁላ፥ ሶማሊያ ራሷን ለመቻል በምታደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ ትብብር እና አጋርነት እንደማይለያት ቃል ገብተዋል።
የጎረቤት ሀገር ሰላም የእኛም ሰላም፣ የጎረቤት ሀገር ሰላም መናጋት የእኛም ስጋት በመሆኑ የጋራ ጠላታችንን እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ ዝግጁ ነን ብለዋል።
የሶማሊያ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አዲዋ የሱፍ ራጌ በበኩላቸው፥ አሸባሪው አልሸባብ በሶማሊያ ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመቀነስ ረገድ በአሚሶም ጥላ ስር ለግዳጅ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰራዊት የማይተካ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
አያይዘውም የሶማሊያን ሰላም ለማስጠበቅ ቃል እየገቡ ከሚሄዱት የውጭ ሀገራት ይልቅ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጎረቤት ሃገራት የሰሩት ተግባር ፅኑ ወዳጅነት በቃላት የሚነገር ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚረጋገጥ መሆኑ ማሳያ መስታወት ነው ብለዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!