አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሐረሪ፣ ምስራቅ ኦሮሚያ፣ ፌደራል ፖሊስና መከላከያን ያካተተው የፀጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ምክክር አድርጓል።
የፀጥታ ምክር ቤቱ ባካሄደው መድረክ የስድስት ወር ግምገማን ጨምሮ በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ፣ ህገ ወጥ የመሳሪያ እና የሰዎች ዝውውርን በተለይም የህግ የበላይነት ማስከበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከሩን ከሐረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የሀረሪ ክልል የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ናስር ዩያ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፥ ባለፉት ስድስት ወራት ከፀጥታ ጋር በተያያዘ አበረታች ተግባራት ቢከናወኑም ችግሮች ተስተውለዋል።
በተለይም ወንጀለኞችን ወደ ህግ ከማቅረብ አንፃር፣ ህገወጥ የመሳሪያ እና የሰዎች ዝውውር እንዲሁም የኮንትሮባንድ ንግድን ከመከላከል አንፃር የበለጠ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከሳምንት በፊትም በክልሉ የጥምቀት በዓል አከባበርን ለማወክና ግጭት ለመፍጠር በተደረገ ሙከራ የሰው ህይወት ማለፉን፣ በሰላማዊ ዜጎችና በፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም በመንግስትና በግለሰቦች ንብረት ጉዳት መድረሱንም ጠቁመዋል።
በክልሉ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳን ለማስፈፀም የሚደረግ እንቅስቃሴ ህገወጥ እና ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም አንስተዋል።
እንቅስቃሴው የህዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በማወክ አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያም ማቅረብ ያልቻለበት ሁኔታ ፈጥሯልም ብለዋል።
በመሆኑም በክልሉ የህዝብን ሰላምና እንቅስቃሴ የሚያውኩ አካላት ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቅሰው፥ የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው በመንቀሳቀስ የህዝቡን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ብሄርንና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንዲሁም በየጊዜው የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ህዝቡ በስጋት እንዲኖር እና በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ ስለሚያደርግ መንግስት የህግ በላይነትን ከማስከበር አንፃር በቁርጠኝነት መስራት አለበትም ነው ያሉት።
የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ወልደማርያም፥ ከቀበሌ ጀምሮ ያለው አመራር ለሰላምና ፀጥታ ስራ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።