የሀገር ውስጥ ዜና

የመኖ አመራረት ዘዴን በመቀየር ከእንስሳት ሃብት የሚገኘውን ምርት ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ

By Tibebu Kebede

August 21, 2021

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመኖ አመራረት ዘዴዎችን በመቀየር ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ዘዴን በመከተል ከእንስሳት ሃብት የሚገኘውን ምርት መጨመር እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በግብርና ግብዓትና ምርት ግብይት ዘርፍ በእንስሳትና ዓሣ ግብዓት አቅርቦትና ግብይት በእንስሳት መኖ አቅርቦትና ግብይት ላይ በሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እንደተናገሩት በመኖ አመራረት ላይ በበቂ ሁኔታ ማምረት ያልተቻለበት ሁኔታ የመኖ አመራረት ዘዴዎችን በመቀየር ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የአመራረት ዘዴ በመከተል ከእንስሳት ሃብት የሚገኘውን ምርት መጨመር ይገባል ብለዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓትና ምርት ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዓይናለም ንጉሴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ እድል እንዳላት ጠቅሰው፥ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ዘርፉ እምቅ አቅም ያለው ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡

ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በግብዓት አቅርቦት ላይ በተለይም በእንስሳት መኖ አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ትኩረት በመስጠት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መግባባት ላይ በመድረስና ሃላፊነቶችን በመውሰድ ጠንከር ያለ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን የእንስሳት መኖ አመራረት ዘዴን ለገበያ የሚሆን የእንስሳት መኖ እንዴት ማምረት ይቻላል የሚለውን ጉዳይ በቀጣይ ልክ እንደ መስኖ ስንዴ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በቀጣይ አመታት ጥሩ የሆነ የእንስሳት መኖ በማምረት በስፋት ለመስራት የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህን ለማሳካት የግል ባለሃብቱን በሰፊው ለማሳተፍ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!