Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዓየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መስፈርትን በመጠበቅ ጥንቃቄ በማድረግ በረራውን ወደ ቻይና እያከናወነ መሆኑን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ተጓዞቹንና የበረራ ሰራተኛዎቹን ዓለም አቀፍ መስፈርትን በተከተለ መንገድ ከኮሮና ቫይረስ ጥበቃ እና ጥንቃቄ በማድረግ በረራውን ወደ ቻይና እያከናወነ መሆኑን ገለፀ።

የዓየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ ከኢትዮጵያ እና ቻይና መንግስታት የሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመስራት የዓለም አቀፉ የዓየር ትራንስፖርት ማህበር እና የዓለም ጤና ደርጅት ባስቀመጡት መስፈርት መሰረት ተጓዦችን እና የበረራ ሰራተኞቹን ከቫይረሱ ለመጠበቅ እየሰራ ነው።

ይህንንም በማድረግ በቻይናውያን የአዲስ ዓመት ወቅት ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደነበረው ወደ አምስቱም የቻይና መዳረሻዎቹ ማለትም ወደ ቤጂንግ፣ ሻንጋይ፣ ጉኧንዡ፣ ቼንጉ እና ሆንግ ኮንግ በረራውን በማድረግ ላይ መሆኑን አቶ ተወልደ አስታውቀዋል።

ቻይና የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ቀደምት መዳረሻ መሆኗን በማንሳትም አሁን ላይ ሀገሪቱን ከመላው አፍሪካ ጋር በዓየር ትራንስፖርት ላለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ማገናኘቱን ተናግረዋል።

አቶ ተወልደ በዚሁ አጋጣሚም የቻይና ህዝብና መንግስት እያደረጉት ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ በማመስገን በዚህ ወቅትም ዓየር መንገዱ ከጎናቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ከታሕሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና ውሃን ከተማ መከሰቱ ይታወቃል።

እስካሁንም በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 170 የደረሰ ሲሆን፥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 7 ሺህ 711 መድረሱ ነው የተገለፀው።

 

Exit mobile version