አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በአፋር ዞን ሶስት እና አርጎባ ብሄረሰብ ልዩ ወረዳ ባሉ መተላለፊያ ቦታዎች የስጋት ቀጠናዎችን በመለየት በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን የየዞኖቹ አመራሮች አስታወቁ።
ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ የመንግስት አመራሮች ከዞን ከወረዳና ከቀበሌ አመራሮች እና የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር በአልዩ አምባ ከተማ መክረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ የህወሓት የሽብር ቡድን ጥቃት መጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የሆኑት የአማራና የአፋር ክልሎች ህልውናቸውን ለማረጋገጥ በጋራ እንዲቆሙ አድርጓቸዋል ብለዋል።
በህዝቡ ውስጥ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ አካላትን ለመቆጣጠር የአፋርን የመረጃ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ብልፅግና ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ብርሃኑ በበኩላቸው፥ ጦርነት የሚጠይቀውን ስነ ልቦና በመታጠቅ የህወሓት እና የኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድኖችን የሰርጎ ገብ እንቅስቃሴ ለመግታት በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ህወሓት በውሸት ትርክት ተለያይተን የነበርን ህዝቦች እንድንሰባሰብና ህብረት እንድንፈጥር አድርጎናል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅረማርያም ደጀኔ ናቸው።
ሃላፊው አያይዘውም ይህንን ትብብር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከድል በኃላ ለልማት ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በአፋር ክልልን የዞን ሶስት ምክትል አስተዳዳሪ እና ፀጥታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብዱ አሊ በአማራ ህዝብ ላይ ሂሳብ አወራርዳለሁ ባለው የህወሓት የሽብር ቡድን ላይ በአፋር ህዝብ ላይ በፈፀመው ጭፍጨፋ ቀድመን በጋራ ሂሳብ እናወራርድበታለን ብለዋል።
አመራሩን ከህወሓት አስተሳሰብ ማውጣት ላይ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም አንስተዋል።
ሃብት ማሰባሰብ፣ ለመከላከያ መመልመል፣ የህልውና ዘመቻውን ተቀላቅለው ወደ ግንባር የዘመቱ የዘማች ቤተሰቦችን መደገፍ ላይም ሊሰራ እንደሚገባ መገለጹን የሰሜን ሸዋ ዞን ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!