Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቱርክ ጉብኝት ስኬታማ ነበር – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቱርክ ጉብኝት ስኬታማ እንደነበር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቱርክ ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ እንደነበር ጠቅሰው፥ ጉብኝታቸው የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሻግር መሆኑን ገልጸዋል።

በጉብኝቱ ወቅትም ሃገራቱ በውሃና በመከላከያ ዘርፎች ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውሰው፥ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገው አቀባበልም የሃገራቱን ጥልቅ ወዳጅነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ጀፍሪ ፊልትማን ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

በወቅቱም በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ እና የችግሩን መንስኤና ችግሩ እንዳይፈጠር መንግስት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም አሜሪካ በኢትዮጵያም ሆነ በቀጠናው ላይ የያዘችው አቋም ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ፥ አሸባሪው ቡድን ከተናጠል የተኩስ አቁሙ ወዲህ በአማራ እና አፋር ክልል ግድያና ሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈፀሙን ገልጸውላቸዋልም ነው ያሉት።

በተጨማሪም በአሜሪካ መንግስት በኩል የታየው ሚዛናዊ ያልሆነ እና የአሸባሪውን ቡድን የሚደግፍ አቋም ተገቢ አለመሆኑን ገልጸውላቸዋል።

አሜሪካ ለሃገራዊ ምርጫው እውቅና አለመስጠቷ፣ አሸባሪው ቡድን አሁን ላይ በአፋር እና በአማራ ክልል እያደረሰ ያለው ጥፋት በአሜሪካ በኩል በዝምታ መታለፋ እንዳሳዘናቸው እና አግባብ እንዳልሆነ መግለጻቸውንም አንስተዋል።

አምባሳደር ዲና ጀፍሪ ፊልትማን ህወሓት በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተጠላ እና የተወገዘ ድርጅት እንደሆነ ማረጋገጣቸውንም ነው የገለጹት።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ጣልቃ ሲገቡ የነበሩ ኃይሎች መንግስት ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ ያለው መሆኑን እያረጋገጡ መጥተዋልም ነው ያሉት።

ጀፍሪ ፊልትማን በበኩላቸው አሜሪካ በቀጠናው ያላትን ትልቅ ሚና ገልጸው በሃገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ የአሜሪካ ፍላጎት መሆኑን መናገራቸውን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያም አስፈላጊው ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከመፈለግ ያለፈ አላማ አሜሪካ የላትም ብለዋል ፊልትማን።

በቆይታቸውም ከሰላም ሚኒስቴር እና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘ መንግስት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፥ በሳዑዲ በኢትዮጵያውያን ላይ የቀጠለው ትንኮሳ እንዲቆም መጠየቁን አውስተዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን ከጅቡቲ፣ ከሱዳን እና ከየመን ዜጎች መምጣታቸውን ጠቅሰው፥ ከየመን 4 ሺህ ዜጎችን ለመለስ የጉዞ ሰነድ መዘጋጀቱን እንዲሁም ከሳዑዲ በሳምን ሶስት ጊዜ በረራ በማካሄድ ዜጎችን የመመለስ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ከመቸውም በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን በማንሳትም፥ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም፣ ለመከላከያ እና የህዳሴ ግድብ ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።

ከውጭ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ አንጻር ቱርክ በኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሃገር መሆኗን ያነሱት ቃል አቀባዩ፥ በውጭ ግንኙነት መርሆዎች መሰረት ዓለም አቀፋዊ ጎራ አለ ብላ እንደማታምንም ጠቁመዋል።

የህዳሴ ግድብ ከሰላምና ጸጥታ አንጻር ቀዳሚ ትኩረት እንደተሰጠውም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የለውጥ ስራዎችን እየተካሄደ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፥ የተመጠነ የሰው ኃይል ያላቸው ውጤታማ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን ማቋቋም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በቻይና እና በአሜሪካ ያሉ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ሊታጠፉ ይችላሉም ብለዋል ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው።
ከኢትዮ ሱዳን ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም ሱዳን በህገ ወጥ ተግባሯ እንደቀጠለች መሆኑን በመጥቀስ፥ የሃገሪቱ ባለስልጣኖች የተጣረሱ መግለጫዎችን እየሰጡ መሆኑን አመላክተዋል።

በወንደሰን አረጋኸኝ እና ፍሬህይወት ሰፊው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version