አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውስትራሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የህልውና ዘመቻን መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ውይይት በማካሄድ ድጋፍ አድርገዋል።
በአውስትራሊያ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር ዶክተር ሙክታር ከድር ወቅቱ የእርሻ ወቅት በመሆኑ፣ የትግራይ አርሶ አደር በተረጋጋ ሁኔታ የእርሻ ተግባሩን እንዲያከናውንና ወደ ፊት ሊያጋጥም የሚችለውን የምግብ እጥረት ስጋት ለማስቀረት፣ እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነትን ለማጠናከር የተናጠል ሰብዓዊ ድጋፍ ተኩስ አቁም መወሰኑን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጅ አሸባሪው የትህነግ ቡድን የተናጠል ተኩስ አቁሙን ለተሻለ ዓላማ ከመጠቀም ይልቅ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተሳሰር ኃይሉን አሰባስቦ ህጻናትን ለጦርነት በመመልመል በአጎራባች የአማራና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቁመዋል።
በዚህም መከላከያ ሰራዊት በወንጀለኛው ቡድን ላይ እርምጃ በመውሰድ የሃገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ተሳታፊዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ብቻ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ታሪካዊ ጠላቶቿ እረፍት የሚነሱ ቡድኖችን በመደገፍ ከወደፊት እርምጃዋ ለመግታት ጥረት እየዳረጉ በመሆኑ ሁሉም በአንክሮ ሊያየው ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ ዳያስፖራው በቀላሉ ገንዘብ ሊያስተላልፍባቸውና የህልውና ዘመቻውን ሊያግዝ የሚችልባቸው ተጨማሪ የኦንላይን ማስተላለፊያ ይፋዊ መንገዶች እንዲመቻቹላቸውና ድጋፉ በተቀላጠፈ መልኩ ለተፈላጊው ዓላማ እንዲደርስ ማድረግ እንደሚገባ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
በዳያስፖራ አደረጃጀቶች የሚያሰባስቡት ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ በእለቱ ከተገኙ ተሳታፊዎች 25 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር መከላከያን ለመደገፍ ቃል የተገባ ሲሆን፣ በርካታ ተሳታፊዎች በየወሩ ከ100 እስከ 300 ዶላር ለአንድ ዓመት ጊዜ በቋሚነት ለመለገስ ቃል ገብተዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!