Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ300 ቢሊየን ብር በላይ የዲጂታል ግብይት ተከናወነ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2013 በጀት ዓመት ከ300 ቢሊየን ብር በላይ የዲጂታል ግብይት መከናወኑ ተገለፀ።

በ2014 በጀት ዓመት የመንግስት አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል እንደሚቀየሩ ነው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያስታወቀው።

የኢኖቬሺንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ÷ሀገራዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን ወደ ስራ የሚያስገቡ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋልም ብለዋል።

በቀጣይ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልውውጡን ህጋዊ የሚያደርጉና ከተለያዩ የመንግስት አሰራሮች ጋር የሚያናብቡ አዋጆችና አሰራሮች ለመተግበር እንዲያስችል ለአቃቤ ህግ መላካቸውም ነው የተገለፀው።

በዘንድሮው በጀት ዓመት አዲሱ ፓርላማ ስራ እንደጀመረ ፀድቆ ቁልፍ የሚባሉ የመንግስት አገልግሎቶች የዲጂታል ኢኮኖሚውን ይቀላቀላሉ ተብሎም እንደሚጠበቅ ተመልክቷል።

በሚኒስቴሩ የዲጂታል ትራንስፖርቴሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጀኔራል ዶክተር አብዮት ባዩ ፤ አሁን ላይ በርካቶች የዲጂታል ኢኮኖሚውን እየተቀላቀሉ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱን ለማህበረሰቡ የማስተዋወቅ ስራም በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰራ ነው የተነገረው፡፡

በሚኒስቴሩ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አያልነህ ለማ በበኩላቸው÷ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን ተከትሎ የኦን ላይን ግብይት መጀመሩ ጊዜና ገንዘብን ከመቆጠብ አልፎ ዝርፊያና ስርቆት የመሳሰሉ ወንጀሎችን ለመከላከል ትልቅ ሚና እንዳለው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዲጂታል ግብይት ስርዓቱ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመቀመር በሚስጥርና በጥንቃቄ የሚከወን መሆኑም ተገልጿል።

ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version