አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት የሽብር ቡድን በአማራና በአፋር ከልል በከፈተው ጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ ማቅረብ አጀንዳቸው ያላደረጉ የተራድኦ ድርጅቶች ተግባር ፖለቲካዊ ሴራቸውን ግልጽ ያደረገ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ሳይንስና የአስተዳደር ምሁራን ድርጅቶቹ በሰብአዊ ስም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ዋነኛ አላማቸው ለመሆኑ ማሳያው የሰሞኑ ተግባራቸው ነው ብለዋል ።
በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ አስተዳደር እና ልማት ኢንስቲቲዩት መምህር ዶክተር መሀመድ አሊ ሰብአዊነት እንደ ፖለቲካ መሳሪያ የመጠቀም ተለምዷዊ ግብራቸውን እያየን እንገኛለን ብለዋል።
በአማራና በአፋር ክልል የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ዜጎች ከመፈናቀላቸው በተጨማሪ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናት ምርምር ማእከል መምህር ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ በበኩላቸው ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው የሚነሳ የራስ ፍላጎት ማስፈጸሚያ በመሆናቸው ሰብአዊነቱ እንዳመቺነቱ ተቀያያሪ ነው ብለዋል ።
በአሁኑ ሰአት በአማራና በአፋር የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለመርዳት የሰብአዊ ኮሪደሩ ምቹ ቢሆንም የፖለቲካ ትርፉ ሚዛኑ አንሶባቸዋልና ዝምታውን መርጠዋልም ብለዋል ምሁራኑ ።
የፌደራል መንግስት ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ህዝባዊ የመረዳዳት ባህል የሚጎለብትበትን ስርአት ማጠናከር እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
በአማራና በአፋር ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮችን በራስ አቅም ለመደገፍም እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አውስተዋል።
በሀይለየሱሰ መኮንን
፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!