አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሀይል ፣ ለሚሊሻ ፣ ለፋኖ እና የክተት ጥሪውን ተቀብለው በማይጠብሪ ግንባር ሽብርተኛውን የህወሓት ቡድን በመፋለም ለሚገኙ ሀይሎች ድጋፍ አደረጉ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በግንባር ተገኝተው ድጋፉን ካስረከቡ በኋላ እንደተናገሩት፥ ህዝቡ ከ83 ሚሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ በሁሉም ግንባሮች ለተሰለፈው ሀይል ድጋፍ አድርጓል ።
በማይጠብሪ ግንባር ለተሰለፈው ሀይልም ለጊዜው 78 የእርድ ከብቶች ፣ 18 ፍየልና በግ ማስረከባቸውንና በቀጣይነትም የህልውና ዘመቻው እስከሚጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የመከላከያ ተቋምን ለማጠናከር የሚደረገውን ርብርብ ለመደገፍ በዞኑ የሚገኙ ወጣቶችን በመመልመል ወደማሰልጠኛ መላካቸውን የተናገሩት አስተዳዳሪው፥ ዞኑ ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር የሚያዋስን እንደመሆኑ አሁን ላይ ካሉ የፀጥታ ስጋቶች አንፃር መላው የዞኑ ህዝብ ኢትዮጵያን ለማዳን ከተሰለፉ ሀይሎች ጋር በፅናት በመቆም ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የምዕራብ ዕዝ ዕደላ ሀላፊ ሌተናል ኮሎኔል አሸብር ሽፈራው በበኩላቸው፥ በግንባር የተሰለፈው ሀይል ህዝቡ እያደረገለት ባለው ድጋፍ ተነሳስቶና በግዳጁ ተግቶ የጁንታውን ግብዓተ-መሬት በማፋጠን ላይ መሆኑን ገልጸዋል ።
ባለፉት ጊዜያት ከኦሮሚያና ከሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች የተላኩትን ድጋፎች ሰራዊቱ በተገቢው እንደተጠቀመ ሁሉ የምዕራብ ጎንደር ዞን ህዝብ ላደረገው አለኝታነት ምስጋና ማቅረባቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!