የሀገር ውስጥ ዜና

በሁመራ ግንባር ሠራዊቱ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ አንደበት ተናጋሪ ሆኖ ጠላትን እየተፋለመ ነው – የአማራ ልዩ ኃይል አዛዦች

By Tibebu Kebede

August 14, 2021

 

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ሕልውና ለመታደግ ከአራቱም አቅጣጫ የመጡት የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት እና የመከላከያ ሠራዊቱ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ አንደበት ተናጋሪ ሆነው ጠላትን እየተፋለሙ መሆናቸውን የአማራ ልዩ ኀይል አዛዦች ገለጹ።

የልዩ ኀይል አዛዦቹ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) እንደተናገሩት በሕግ ማስከበር ዘመቻው የነበረውን አንጸባራቂ ድል በሕልውና ዘመቻው ለመድገም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

አዛዦቹ እንዳሉት የአማራ ልዩ ኀይል ከመከላከያ ሠራዊትና ከሚሊሻ አባላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር በሕግ ማስከበር ዘመቻው አሸባሪው ትህነግን ድባቅ በመምታት ሀገርን በልዩ ወታደራዊ ብቃት ታድጓል፡፡

አሁንም እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው የኢትዮጵያን ሕልውና ለመታደግ በሁመራ ግንባር የትህነግን አሸባሪ ሃይል በመፋለም ላይ ናቸው።

ሻምበል ደሳለኝ አምባው የተከዜ ወንዝን ተከትሎ እንደንብ ከሰፈረው የአማራ ልዩ ኀይል መካከል የአንድ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ናቸው፡፡

ለረጅም ዓመታት በውትድርና ሙያ እንዳሳለፉ የሚናገሩት ሻምበል ደሳለኝ የአሸባሪው ትህነግ ቡድን አባላት ከመንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በኋላ በአካባቢው 11 ጊዜ ውጊያ መክፈታቸውን ተናግረዋል፡፡

“አሸባሪው ቡድን በውትድርና ሕይዎቴ አንድም ቀን አይቸው የማላውቀው አይነት ጦርነት ሲከፍት አስተውያለሁ” የሚሉት ሻምበል ደሳለኝ፣ ስምሪታቸው ከወታደራዊ ሳይንስ እና ስልት ውጭ ግብዝነት የተሞላበት ነው ይላሉ፡፡

ምክትል አዛዡ እንደሚሉት እስካሁን በተደረጉት ውጊያዎች የተረዱት አሸባሪው ትህነግ ለጦርነት የሚልካቸው ቡድኖች ምንም አይነት መሰረታዊ የውትድርና እውቀት የላቸውም።

ወደ ጦርነት መሰማራት ቀርቶ ጦርነት በሚደረግበት አካባቢ መኖር የማይገባቸው ሕጻናት የጦርነቱ ፊታውራሪ ሆነው ሲመጡ እንደማየት አሳዛኝ ድርጊት አይኖርም ነው ያሉት ሻምበል ደሳለኝ፡፡

በሁመራ ግንባር ከተሰማራው የአማራ ልዩ ኀይል የአንድ ሻምበል ምክትል አዛዥ የሆኑት ዋና ሳጅን ግርማ በላይ እስካሁን በተደረገው የአሸባሪው ትህነግ ቡድን ተደጋጋሚ ጦርነት ተከዜን መሻገር የቻለ የለም ብለዋል።

በአካባቢው በተደረገው ጦርነት አሸባሪው ትህነግ የተዋጋው በወታደራዊ ሳይንስ በተካነ መንገድ ሳይሆን ሃሽሽ ስንቁ እና ትጥቁ ባደረገ ቡድን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

“በየትኛውም ዓለም በተደረገ ጦርነት የማይተኩስ ነገር ግን ወደ ጠላት ምሽግ ሰተት ብሎ ለመግባት የሚሞክር ተዋጊ አልተሰማም” የሚሉት ዋና ሳጅን ግርማ ፣ ሕጻናትን በሃሽሽ አደንዝዞ መላክ የሽብር ቡድኑ የፈጸመው ይቅር የማይባል ታሪክ ወንጀል ነው ይላሉ፡፡

ተከዜን መሻገር የአሸባሪው ቡድን የቀን ቅዥት ነው የሚሉት አዛዦቹ ፤ በአካባቢው የተሰማራው የአማራ ልዩ ኀይል እና ሕዝባዊ ሠራዊት በሕግ ማስከበር ዘመቻው ያሳየውን የላቀ ግዳጅ አፈጻጸም በሕልውና ዘመቻው እንደሚደግመው ተናግረዋል፡፡

ሕዝቡ ለሠራዊቱ ደጀን መሆኑን በተግባር እያሳየ መሆኑን የገለጹት የልዩ ኀይል መሪዎቹ፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!