አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሃት እና ሽኔ ያደረጉት የጋራ ስምምነት የቡድኖቹን ድብቅ የሽብር ተግባር ያጋለጠ አጋጣሚ ነው አሉ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፡፡
የሽብር ቡድኖቹ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አብረው መስራታቸው አሳፋሪና የሚኮነን ተግባር መሆኑን ነው ምሁራኑ ለኢዜአ የተናገሩት፡፡
መንግስት እነዚህን የጥፋት ቡድኖች እኩይ ተግባር በመረጃ በማስደገፍ በሽብር እንዲፈረጁ ማድረጉ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን የአሁኑ ጋብቻቸው አመላካች ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከምሁራኑ መካከል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር መሐመድ ጀማል የቡድኖቹ የጋራ ስምምነት ከዚህ በፊት በድብቅ ሲያካሄዱ የነበረውን የሽብር ተግባር ገሃድ ያወጣ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ከዚህ በፊት ህወሃትና ሸኔ በድብቅ ሀገርን ለማፈራረስ እየሰሩ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ለህዝቡ ግልጽ በማድረግ በሽብር እንዲፈረጁ ማድረጉም ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ዶክተር መሐመድ ገልጸዋል፡፡
መንግስት ሀገሪቱን ለማዳን እየወሰደ የሚገኘው የህልውና ዘመቻ በስኬት እስኪጠናቀቅ መከላከያ ሰራዊቱንበመደገፍም ሆነ ህብረተሰቡ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኝ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ነው የገለጹት፡፡
ህወሃት በተለይ ሸኔን በመጠቀም በኦሮሚያ የሽብር ተግባሩን ሲያከናውን መቆየቱን በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተደረሰው የጥፋት ስምምነቱ ትልቅ ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲ ምሁር አቶ ሌንጮ ሳሙኤል ናቸው፡፡
አቶ ሌንጮ እንዳሉት ይህ ህዝብን እያጭበረበረ የሚገኘውን የሽብር ቡድን ዕኩይ ተግባር በመረዳት አንድ ሆነን በምንችለው ሁሉ ልንታገለው ይገባል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ሸኔን ለአፍራሽ ተልዕኮው እንደሚጠቀምበት ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በንጹሃን ዜጎች ላይ ከፈፀመው ጥፋት መረዳት እንደሚቻል የገለጹት ሌላው የዩኒቨርሲቲው ምሁር አባቦ ግርማ ናቸው፡
በሽብር ቡድኖቹ ጥምረት ሳንደናገጥ ሀገርን ለማዳን የተጀመረውን የህልውና ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ የጀመርነውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን