Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የደሴ ህዝባዊ መጅሊስ በአሸባሪው ህወሃት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አቀረበ

 

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ደሴ ከተማ አስተዳደር ህዝባዊ መጅሊስ በአሸባሪው ህወሃት ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ከ700 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የመጅሊሱ ፕሬዝዳንት ሸህ እንድሪስ በሽር ድጋፍ ሲያደርጉ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሃት በከፈተው
የሽብር ጦርነት ከሞቀ ቤት ጎጇቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍ ከሁሉም ህብረተሰብ ይጠበቃል፡፡

መጅሊሱ ህብረተሰቡን በማስተባበር የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በተደረገው እንቅስቃሴም ከ700 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

ከተደረገው ድጋፉ መካከልም 100 ኩንታል ዱቄት፣ 100 ብርድ ልብስ፣ 100 ምንጣፍና ሌሎችም እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ አካባቢውንና አንድነቱን ጠብቆ ተፈናቃዮችን መደገፍና አሸባሪውን ህወሃት መመከት ይኖርበታል ያሉት ሸህ እንድሪስ ፣ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሰይድ የሱፍ በበኩላቸው ህዝባዊ መጅሊሱ ህብረተሰቡን አስተባብሮ ያደረገው ድጋፍ የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል፡፡

ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው በደሴ ከተማ የተጠለሉ ዜጎች ቁጥር ከ55 ሺህ ማለፉን ጠቁመው፤ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ለማቅረብ ጥረት እያረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ተፈናቃዮቹም ህብረተሰቡ የእለት ደራሽ ምግባቸውን እያቀረበላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ የደሴ ህዝባዊ መጅሊስ ላደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና ማቅረባቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version