አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሠራዊትንና የሶማሊ ክልል ልዩ ሀይል የሚደግፍ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተካሄደ።
በሰልፉ ላይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ እና ምክትል ርዕሠ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን እንዲሁም ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በጅግጅጋ ከተማ እስታዲየም በተካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የከተማው ነዋሪዎች ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍና አሸባሪውን የህወሓት ጁንታ የሚያወግዙ የተለያዩ መልክቶችን አስተላልፈዋል።
በጅግጅጋ ከተማ ከሚገኙ 20 ቀበሌዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ በመውጣት አሸባሪውን የህወሓት ጁንታ ቡድን ሀገር የማፍረስ ተግባር የሚቃወምና የሀገር መከላከያ ሠራዊትንና የሶማሊ ክልል ልዩ ሀይልን የሚደግፍ የድጋፍ ሰልፍ ነው ያካሄዱት፡፡
የከተማው ነዋሪዎች የተለያዩ መፈክሮችን አንግበው ለመከላከያ ሠራዊትና ለሶማሊ ልዩ ሀይል ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ባለፉት 30 አመታት በሶማሊ ክልል ህዝብ ላይ የፈፀመው አስከፊ በደሎች ከህሊናችው መቼም እንደማይጠፋ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለረጅም ጊዜ ሲሰራ የቆየውን ኢትዮጵያዊያን የማፍረስ እቅድ ለማሳካትና ዳግም የማእከላዊ መንግስት ስልጣን ላይ ለመውጣት የተለያዩ የጥፋት ተግባር እየፈፀመ ነው ብለዋ፡፡
ጁንታው ሀገር የማፍረስ አቅም የለውም ያሉት የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ይህንን የጥፋት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብአተ መሬቱን በመፈፀም የሀገሪቱን ሰለም ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የሶማሌ ህዝብ ባለፉት 30 አመታት በጁንታው የተጎዳ ህዝብ መሆኑን የጠቆሙት ርእሰ መስተዳደሩ የክልሉ ህዝብ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለማጥፋት ከመላው የሀገሪቱ ህዝብ ጎን ተሰልፎ የሚጠበቅበትን ተጋድሎ ያደርጋል ብለዋል።
ወቅቱ የመላው የሀገሪቱ ህዝቦች አንድነት የሚያስፈልግበት ወቅት በመሆኑ ህብረተሰቡ በየአከባቢው ግጭትና መከፋፈል የሚፈጥሩ ሀይሎችን እኩይ ሴራ በማክሸፍ በፍቅርና በአንድነት መንቀሳቀስ እንደሚገባ መናገራቸውን የሶማሊ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!