Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጎግል የቻይና ቢሮውን በጊዜያዊነት ዘጋ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጎግል በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በቻይና የሚገኘውን ቢሮውን በጊዜያዊነት መዝጋቱን አስታወቀ።

የመረጃ ማፈላለጊያ ገጹ ከቻይና በተጨማሪ በሆንኮንግ እና ታይዋን የሚገኙ አገልግሎት መስጫ ቢሮዎቹን መዝጋቱንም አስታውቋል።

ከጎግል በተጨማሪ አማዞን እና ማይክሮሶፍትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሰራተኞቻቸውን ደህንነት ለመጠበቅ በሚል ተመሳሳይ እርምጃ ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።

ጎግል ሰራተኞቹ ወደ ቻይና እና ሆንግ ኮንግ ከሚያደርጉት ጉዞ እንዲታቀቡና በቻይና የሚገኙትም በተቻለ ፍጥነት እንዲወጡ መምከሩም ተነግሯል።

ባለፈው ሳምንት ፌስቡክ ሰራተኞቹ ወደ ቻይና እንዳይጓዙ ያስጠነቀቀ ሲሆን፥ ተሽከርካሪ አምራቹ ጄኔራል ሞተርስም ፋብሪካዎቹን ዘግቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የጃፓኑ ቶዮታ እስከ ፈረንጆቹ የካቲት 9 ድረስ በቻይና አገልግሎት መስጠት ማቆሙን አስታውቋል።

የፈረንሣዩ ፒ ኤስ ኤ እንዲሁም የጃፓኖቹ ሆንዳ እና ኒሳን ሰራተኞቻቸውን ከቻይና የማስወጣት እቅድ እንዳላቸው ተነግሯል።

ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘባት ውሃን ከተማ መቀመጫቸውን ያደረጉ ዓለም አቀፍ አምራቾችም ሰራኞቻቸውን ከቻይና ማስወጣት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ውሃን የቻይና ሰባተኛ ትልቋ ከተማ እና ዋነኛ የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያዎች መቀመጫ ናት።

ምንጭ፦ ቢ.ቢ.ሲ

Exit mobile version