ቢዝነስ

አምራች ኢንዱስትሪውን በማበረታት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

By Alemayehu Geremew

August 10, 2021

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት መፋጠን የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የጎላ በመሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለማበረታታት እየተሰራ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ መንግስት ቀጥተኛና ቀጥታኛ ያልሆኑ የማበረታቻ ሥርዓቶችን ዘርግቶ ዘርፉን በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ የኢኮኖሚውን እድገት ለማፋጠን ያስችለዋል ነው ያለው፡፡

ከውጪ የሚገቡ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱና ለሚሸጡ ባለሀብቶች በተመረጡ ዘርፎች የታሪፍ ከለላ የሚሰጥበት ለአንድ ዓመት የሚቆይ የሁለተኛ መደብ የጉምሩክ ታሪፍ ሀ ሰርቴፍኬት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም የተመላሽ ቀረጥ፣ የቫውቸር፣ የቦንድድ ኤክስፖርት ፋብሪካ፣ የቦንድድ ኤክስፖርት ማምረቻ መጋዘንና የቦንድድ ግብዓት አቅርቦት መጋዘን የቀረጥ ማበረታቻ ስርዓቶች ተዘርግተው በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን የመደገፍና የማበረታት ስራ እየተሰራ እደሚገኝም ተገልጿል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት ለ 21 ድርጅቶች አዲስ የቫውቸር ስርዓት ተጠቃሚነት ሠርተፊኬት በመስጠትና ለ82 ድርጅቶች የቫውቸር ዕድሳት በማድረግ ከ180 ሚሊየን ብር በላይ ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ነጻ ግብአቶችን እንዲያስገቡ መደረጉም ተመላክቷል ፡፡

በሌላ በኩል ለ15 አምራች ኢንዱስትሪ ድርጅቶች የሁለተኛ ታሪፍ ምድብ ሀ አዲስ ሠርተፊኬት መሰጠቱንና እና ለ56 ድርጅቶች ሰርተፍኬታቸው መታደሱ ነው የተገለጸው፡፡

በበጀት ዓመቱ በማበረታቻ ስርዓቱ ከውጭ እንዲገቡ ከተደረጉት የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ውስጥ 70 በመቶ ያህል ተመርቶ ለውጭ ገበያ መቅረቡን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!