አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት112 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገለጸ፡፡
ኮሚሽኑ 125 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ነው 112 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሰብሰብ የቻለው፡፡
በዚህም የእቅዱን 89 ነጥብ 58 በመቶ ማሳካት መቻሉ ነው የተገለጸው፡፡
ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸርም የ7 ነጥብ 12 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ለገቢ አሰባሰቡ ውጤታማነት እንቅፋት የሆኑ ሀገራዊ ፈተናዎች በተጋረጡበት ወቅት ቢሆንም በተደረጉ የአሰራር ስርአት ማሻሻያዎችና ህጎች፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን መተግበርና ሌሎች በርካታ የለውጥ ስራዎች ለእቅዱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ ወደ ተለያዩ ሃገራት ከተላኩ ቡና፣ አበባ፣ ጫት እና ሌሎች የወጪ ምርቶች ሽያጭ ከ 3 ቢሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ነው የተገለፀው፡፡
የገቢ እና ወጪ ኮንትሮባንድ መከላከል፣ የተገልጋይ የአገልግሎት እርካታን ማሳደግ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ ልማትና አጠቃቀም በዓመቱ ውጤታማ ስራ የተሰራባቸው ዘርፎች ናቸው ተብሏል፡፡
የተገልጋዩን የህግ ተገዥነት ለማረጋገጥ ውጤታማ ስራ በመሰራቱ በበጀት አመቱ ከኮንትሮባድ ቁጥጥር 37 ቢሊየን ብር ማዳን መቻሉ ተመላክቷል፡፡
ይህም ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ44 በመቶ እድገት ማሳየቱ ነው የተገለፀው፡፡
ኮሚሽኑ በ2014 በጀት ዓመት 155 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!