አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም መድረክ ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን አቋሞች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በማንጸባረቅ ለሚታወቁት የዓረብ ሃገራት ግንኙነት ተመራማሪ እና ተንታኝ ዛሒድ ዘይዳን አል-ሀረሪ በሀረሪ ክልል የእውቅና እና የምስጋና መርሃ-ግብር ተካሄደ።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት ታታሪነትና ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በሀገር ፍቅር ስሜት ህዝብንና ሀገርን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ አስተዋፅኦ ማበርከትም ነው፡፡
“ከዚህ አንፃርም አቶ ዛይድ ዘይዳን አል-ሐረሪም ሀገር ወዳድነቱን በተግባር እያሳየ ይገኛል” ብለዋል።
“የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እንዳይጠናቀቅ እና ኢትዮጵያ ከድህነት እንዳትወጣ በተለያዩ የውጪ ሃይሎች እየተደረጉ ያሉ ጫናዎችን ለመመከት በራስ ተነሳሽነት በዲፕሎማሲና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል” ነው ያሉት፡፡
በተለይም ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአረብኛ ቋንቋ የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎችን ከማክሸፍ አንፃር በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በመቅረብ እንዲስተካከሉና የአረቡ ዓለም ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነውም ብለውታል።
የአረብ ሀገራት ግንኙነት ተመራማሪና ተንታኝ አቶ ዛይድ ዘይዳን አል-ሐረሪ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር “ሀገሬን እና ህዝቤን እወዳለሁ ፤ ባለኝ ክህሎትና እውቀት ሀገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።
እያከናወኑት ባለው ተግባርም በርካታ ጫናዎችና ማስፈራራት ሲደርስባቸው መቆየቱን አንስተው ሆኖም ግን ለሀገርና ለህዝብ ሲሉ መስዋዕትነት ለመክፈል በመዘጋጀት በስራቸውን በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሆነ መናገራቸውን የሃረሪ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!