አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርባ ምንጭ ከነማ ስፖርት ክለብን ህዝባዊ መሠረት ለማስያዝና የገንዘብ አቅሙን ለማጠናከር በአርባ ምንጭ ከተማ የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ ።
ክለቡ በ2014 ዓ.ም በሚደረገው የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተፎካካሪ እንዲሆን ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።
የአርባ ምንጭ ከነማ ስፖርት ክለብ የበላይ ጠባቂ እና የጋሞዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ የጎዳና ላይ ሩጫው ክለቡ የህዝብ መሆኑን ለማረጋገጥ የተዘጋጀ መርሃ-ግብር ነው ብለዋል፡፡
ክለቡ ከዚህ ቀደም በተወሰኑ ደጋፊ አባላት፣ በዞኑ እና በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር መንግስት ብቻ ይደገፍ እንደነበር የተናገሩት አቶ ብርሃኑ በቀጣይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለክለቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክለቡ ፕሬዚዳንት እና የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰብስቤ ቡናቤ በበኩላቸው የጎዳና ላይ ሩጫው ክለቡን ወደነበረበት ከፍታ ለመመለስና በውድድሩ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀጥል ገቢ ለማሰባሰብ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአርባ ምንጭ እግር ኳስ ክለብን ለማጠናከር ጠንካራ ቦርድ፣ የደጋፊ ማህበር እና ፅህፈት ቤት እንዲኖረው ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
ክለቡን ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ እና በሀገር አቀፍ ብሎም በአህጉር ደረጃ ተፎካካሪ ክለብ እንዲሆን ለማድረግ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአርባ ምንጭ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው፥ ክለቡ ወደ ፐሪሚየር ሊግ መመለሱን ተከትሎ የነበሩበትን ችግሮች በሙሉ የመቅረፍ ስራ እየተከናወነ ነው ማለታቸውን የጋሞ ዞን መንግስት ኮሙዩንኬሽን ጉዳዮች መምሪያ መረጃ ያመላክታል፡፡