የሀገር ውስጥ ዜና

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት መሞከር ተቀባይነት የለውም አለ

By Tibebu Kebede

August 06, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረገው ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ዛሬ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የተደረገላቸው የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላቱም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ መረዳታቸውንና ለኢትዮጵያ አንድነትና ጥንካሬ መቆም እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ሊቀመንበር ዶክተር ራሔል ባፌ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክቶ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ማብራሪያ መሰጠቱን አስረድተዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረግ የአሉታዊ ጣልቃ ገብነት ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለው ማስረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የኢትዮጵያውያን እንጂ የሌላ አለመሆኑን ማስረዳታቸውን የገለጹት ዶክተሯ በዚህ ጉዳይ መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም እንደሚያራምዱ ማስታወቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ አገሪቷ ካለችበት ችግር በፍጥነት እንድትወጣ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወትና ለዚህም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም ምክር ቤቱ ጥሪ ማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባከበር መልኩ በሠብዓዊ ድጋፍና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር መስራት የሚቻል መሆኑንም አብራርተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ከመጠበቅ አንጻር ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ግልጽ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!