አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ዌልስ 20 ሺህ አነስተኛ የካርበን ልቀት መጠን ያላቸውን መኖሪያ ቤቶች ልትገነባ ነው፡፡
የዌልስ የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷ የቤቶቹ ግንባታ እስከ ፈረንጆቹ 2026 ተጠናቆ ለዜጎች በኪራይ ይተላለፋል፡፡
የቤቶቹ ግንባታ ለአካባቢ አየር ተስማሚ የሆነ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት ታሳቢ ተደርጎ እንደሚሰራም ነው የተመላከተው፡፡
እቅዱ ተግባራዊ ሲሆን ለሺህዎች የስራ እና የስልጠና እድል እንደሚፈጥር ታውቋል፡፡
ቤቶቹ ከፀሃይ ኃይል በሚመነጭ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ከራሳቸው አልፈውም ሌሎች የሀገሪቷን አካባቢዎች የኃይል አቅርቦት ፍላጎት እንደሚሸፍኑ ነው የተገለፀው፡፡
የዌልስ መንግስት ሁሉም ቤቶች ጥራታቸውን የጠበቁና የአካባቢ አየር ላይ ጉዳት የማያደርሱ ይሆናሉ ነው ያለው፡፡
እሳቤው አዲስ እና በቀጣይ የሚገነቡ ቤቶች የአካባቢን ብክለት ከመቀነስ አንፃር ታሳቢ ተደርጎ እንዲገነቡ አመላካች ሁኔታን የፈጠረ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ምንጭ÷ ቢቢሲ