Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ታፍ ኦይል ኢትዮጵያ በ450 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የነዳጅ ዴፖ አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታፍ ኦይል ኢትዮጵያ በ450 ሚሊየን ብር ወጪ በኢትዮጵያ አየር መንገድ  ግቢ ያስገነባውን 6 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ መያዝ የሚችል የነዳጅ ዴፖ ዛሬ አስመረቀ።

የአውሮፕላን ነዳጅ ማከማቻ ዴፖው ግንባታ ሁለት ዓመታትን ፈጅቷል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየስ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሄር፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እስክንድር አለሙና የኩባንያው ፕሬዚዳንት አቶ ትንሳኤ አክሊሉ የነዳጅ ዴፖውን በይፋ መርቀውታል።

ዴፖው በአቬሽን ኢንዱስትሪ የአፍሪካ ኩራት ለሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድና መዳረሻቸውን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለሚያደርጉ አየር መንገዶች ነዳጅ በብቃት ማድረስ ያስችላል ተብሏል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየስ፥ አየር መንገዱ ራሱን ከወቅቱ ጋር በማዘመንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ በመሆን የኢትዮጵያን ስም ከፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

የተገነባው የነዳጅ ዴፖ ለአየር መንገዱ አውሮፕላኖችም ሆነ መዳረሻቸውን በዚህ ለሚያደርጉ አየር መንገዶች በአስተማማኝ ሁኔታ ነዳጅ በማድረስ ሀገሪቷንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሄርም የሀገሩን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ ላደረገው አየር መንገድ የተገነባው የነዳጅ ዴፖ ለኢንዱስትሪው ተጨማሪ አቅምና ጉልበት ነው ብለዋል።

ታፍ ኦይል በአገር ውስጥ የዘርፉ አንቀሳቃሾች የተመሰረተና ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን የስራ ዕድል በመፍጠር እየሰራ ያለ ኩባንያ መሆኑን ጠቅሰው ከፍተኛ የደህንነት ጥንቃቄ በሚሻው በዚህ ዘርፍ ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገሪቷ የአቪዬሼሽን ኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን መንግስት ለሚሰራው ስራ አጋዥ ለመሆን በዘርፉ ተሰማርተው ለአገርና ለህዝብ ለሚሰሩ ተቋማት ድጋፍ እንደሚደረግም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እስክንድር አለሙ ድርጅታቸው አየር መንገዱ የአፍሪካ ኩራት ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

የአቪዬሽን ነዳጅ ማደያ እንዲኖር ከዚህ ቀደም ከሌሎች አቅራቢዎች ጋር ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው በአይነቱ ግዙፍ የሆነው የነዳጅ ዴፖ የአየር መንገዱን የአፍሪካ ኩራትነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የኩባንያው ፕሬዚዳንት አቶ ትንሳኤ አክሊሉ በበኩላቸው የዴፖው ግንባታ 350 ለሚጠጉ ሰራተኞች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚጠይቀው በዚህ ዘርፍ በተለይም ደግሞ በአቬሽን ኢንዱስትሪ ተቀላቅለው የብልጽግና ጉዞው አካል በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል።

ታፍ ኦይል ኢትዮጵያ በ2004 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በአገሪቷ ከ74 በላይ የነዳጅ ማደያዎች አሉት።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Exit mobile version