አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሰጠ።
የስታዲየም እና የስፖርት ማዕከል መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታውን ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች ማስረከባቸውን የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሰክሬታሪ መረጃ ያመለክታል።
ኢንጂነር ታከለ ኡማ በዚሁ ወቅት፥ ክለቦቹ የከተማዋ አምባሳደር ከመሆናቸውም ባለፈ በስፖርታዊ ጨዋነት እና በከተማዋ ሁለንተናዊ ሰላምን በማረጋገጥ ወንድማማችነትን በመስበክ የበኩላቸው ሚና እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
ሁለቱ ክለቦች ለከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጎለብት እና ወጣቱ ከአልባሌ ስፍራዎች እንዲቆጠቡ ለሚያርጉት ተግባራት የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያርግም ተናግረዋል።
በነገው እለት ለሚካሄደው የሁለቱ ክለቦች የ11ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ የደርቢ ጨዋታ ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መንገድ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለሁለቱም ክለቦች መልካም እድል ምኞት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አመራሮች በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለስታዲየም መገንቢያ ከመሬት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረጉ በደጋፊዎቻቸው እና በእግር ኳስ ክለቦቹ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።