ጤና

የማሽተት ችሎታን ማጣት በግል ግንኙነትና አካላዊ ጤንነት ላይ  ችግሮች ያመጣል -ጥናት

By Tibebu Kebede

January 28, 2020

አዲስ አበባ፣ጥር 19፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በብሪታኒያ በተጠና አዲስ ጥናት የማሽተት ችሎታቸውን ያጡ ሰዎች በግል ግንኙነታቸውና አካላዊ ጤንነታቸው ላይ ችግሮች ሊያጋጥማቸው እንደሚችል  ጥናት አመለከተ፡፡

የማሽተት ችሎታቸውን ያጡ ሰዎች የንፅህና ችግር ፣ የቀረበ ቅርርብ ፣ እና  አካላዊ ጤንነት ላይ ችግሮች  ሊያጋጥሟቸው  እንደሚችል ጥናቱ አመላክቷል፡፡

የቀን ተቀን ህይወታቸው ላይ ተጽእኖ ከመፍጠሩም በተጨማሪ  በድብርት፣ጭንቀትና ከሰው መገለል የመሳሰሉት ችግሮች ተጋላጭ  እንደሚያደርጋቸው ተገልጿል፡፡

በጥናቱ  የማሽተት ችሎታቸውን ያጡ እድሜያቸው ከ 31 እስከ 80 የሆነ  71 ሰዎች የተካተቱ  ሲሆን÷ ኢንፌክሽኖች ፣ ጉዳቶች  እና የነርቭ በሽታዎችን ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች የማሽተት ችሎታን ለማጣት ምክንያት መሆናቸው  በጥናቱ ተመላክተዋል፡፡

ምግብ ማሽተት አለመቻል  እና በአካባቢ ያለን ቃጠሎ ወይም ጭስ  አለማሽተት በማኅበራዊ ኑሮ ህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከመፍጠሩ ባሻገር ደህንነታቸውን አደጋ ላይ ይጥላል ተብሏል፡፡

በጥናቱ ከተካተቱት ሰዎች መካከል ተወሰኑት የምግብ ፍላጎታቸው ቀንሶ ክብደታቸውን እንዳጡ ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል ያሉት ደግሞ በስብ ፣ በጨው እና ከፍተኛ የስኳር መጠን ያላቸው ምግቦችን በመመገብ  ክብደታቸው መጨመሩ ተመላክቷል፡፡

ይህ ችግር የሚያጋጥማቸው ሰዎች በግል ንጽህና ዙሪያ ጥሩ ስሜት አለመኖር ፣የፍቅር ግንኙነት መቋረጥ  እና አካላዊ የጤና ችግር ይስተዋልባቸዋል ተብሏል።

ተመራማሪዎቹ ጥናቱ ለጉዳዩ  ትኩረት እንዲሰጡና ለታካሚዎች የተሻለ ድጋፍ እና እርዳታ እንዲያደርጉ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡-upi.com