ቴክ

ልናዳብራቸው የሚገቡ የአይ.ሲ.ቲ ክህሎቶች

By Meseret Awoke

July 26, 2021

አዲስ አበባ ፣ሃምሌ 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ልናዳብራቸው የሚገቡ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ክህሎቶች ምንድን ናቸው?

ምንም እንኳን ቴክኖሎጂ የተቋማትን የአሰራር ስርዓት በማዘመን ውጤታማነትን በቃላሉ እንዲያገኙ ያስቻለ ቢሆንም አሁንም ብዙ ድርጅቶች እና ኩባንያዎች ቴክኖሎጂን በተሟላ ሁኔታ የሚተገብሩበት ሂደት አልተጀመረም፡፡

በኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ውስጥ የሚጠቃለሉትን እንደስልክ፣ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ያሉ ቀድምት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደ አይ.ሲ.ቲ ክህሎቶች የሚቆጠሩ ቢሆንም በዚህ ላይ ዘመናዊው ክህሎት የማይታከልበት ከሆነ የተሟላ የአይ.ሲ.ቲ ክህሎት ሊባል አይችልም፡፡

አሁን ላይ ሁሉም ዘርፍ ሊባል በሚችል መልኩ የተሟላ የአይ.ሲ.ቲ ክህሎቶችን የሚፈልግበት ጊዜ ሲሆን፥ ሂደቱም ቴክኒካል እና ቴክኒካል ባልሆነ መንገድ ሊፈፀም እንደሚቻል ከቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ መጠቀም

ምንም አይነት ሚና ይኑረን አሁን ባለው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የአይ.ሲ.ቲ ስርዓት ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ እና ልናተርፍበት በምንችለው መንገድ ካልተጠቀምነው ብዙ ነገር እያጣን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መረጃን የማጋራት አቅም፣ ከደንበኞች ጋር የመወዳጀት እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ተግባራቶችን ለማከናወን የዚህ ክህሎት አስፈላጊነት እንዲህ በቀላሉ አይገለፅም፡፡

. መረጃን የማደረጃት ክህሎት

እንደ ኤክሴል ያሉ የመረጃ ማደራጃ ወይም (Spreadsheet) መተግበሪያዎችን እንደየሁኔታው መጠቀም እና ስራ ላይ ማዋል ከተማሪዎች አንስቶ በተቋማት ውስጥ ተቀጥረው እስከሚሰሩ ሰራተኞች ድረስ ይህ ክህሎት እጅግ ዘመናዊ እና መሰረታዊ ከመሆኑም ባለፈ የስራ ምርታማነትን ለማምጣትም እጅግ ወሳኝ የሚባል ነው፡፡ መረጃን ተንትኖ እንደአስፈላጊነቱ አደራጅቶ ማስቀመጥ የምንሰራውን ስራ በቀላሉ ለማጎልበት እና ደካማ ጎኑን ለይቶ ላመስቀመጥ በእጅጉ ይረዳል፡፡

ፅሁፍ የማቀናበር እና የአቀራረብ ችሎታ

ብዙ ነገሮች በዲጂታል መንገድ በሚፈፀሙበት እና አብዛኞቹ የማንዋል ስራዎች እየቀሩ በመጡበት በአሁኑ ሰዓት ፅሁፍን በሚገባ አቀናብሮ በዲጂታል መሳሪያዎች ማስቀመጥ እና ሌሎች አስፈላጊ የቴክኒካል ዝርዝሮችን አሟጦ መጠቀም በዘመናዊው የአይ.ሲ.ቲ ክህሎት በቀዳሚነት የሚቀመጥ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የዲጂታል መሳሪያዎችን በመጠቀም የአቀራረብ ክህሎቶችን ማዳበር እና የተሻለ ስልት መተግበር በዚህ ሂደት ውስጥ በዋናነት የሚካተት ነው፡፡

. የኪቦርድ አጠቃቀም እና የመተየብ ፍጥነት

ሁሉንም የኪቦርድ አማራጮች በሚገባ መረዳት እና በፍጥንት ሊያሰሩ የሚችሉትን ቀላል አማራጮች በስራ ላይ ማዋል ሌላው መሰረታዊ የአይ.ሲ.ቲ ክህሎት ነው፡፡ ይህን በማድረግ ሂደት የመተየብ ፍጥነታችን ሌላው ተያያዥ ክህሎት ሲሆን፥ የምንሰራውን ስራ በፍጥነት ለማጠናቀቅ እና የተሻለ ውጤት እንድናስመዘግብም በእጅጉ የሚረዳን ነው፡፡

. የኦንላይን ምርምር እና የኢሜል አጠቃቀም

የተለያዩ የመፈለጊያ መሳሪያዎችን ተግባር ላይ በማዋል ስለምንሰራው ስራ ተጨማሪ መረጃዎችን ማፈላለግ እና በበየነ-መረብ አማካኝነት ቀላል ምርምሮችን መካሄድ በአይ.ሲ.ቲ ክህሎት ላይ በዋናነት የሚካተት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንደ ኢሜል፣ ጎግል እና ሊንኪድን ያሉ ግላዊ የመገናኛ አካውንቶችን በመፍጠር መሰረታዊውን የመላላክ ሂደት መጀመር እና ስራዎችን በዚህ መሳሪያ ለመስራት መሞከር ሌላው የአይ.ሲ.ቲ ክህሎት ነው፡፡

. ከለውጦች ጋር ራስን ማሻሻል

በምንጠቀማቸው እያንዳንዱ ቴክኖሎጂዎች እና የአይ.ሲ.ቲ ክህሎቶች ላይ አዳዲስ ነገሮች ሲጨመሩ ራስን በማስተማር እና ሁሌም ዝግጁ በመሆን ከጊዜው ለውጥ ጋር እራስን አብሮ ማስኬድ መሰረታዊ ነው፡፡ ያለ አዳዲስ ክህሎቶች ስራን በፍጥነት ለመስራት እና ተፈላጊውን ውጤት ማምጣት ስለማይቻል ራስን ለአዳዲስ ለውጥ ዝግጁ ማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!