አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀብል የተሰኘችው የአሜሪካ የጠፈር ቴሌስኮፕ ኮምፒውተሯ ላይ በደረሰ እክል ስራ ካቆመች ወዲህ በዘርፉ ኢንጅነሮች ጥገና ተደርጎላት እንደገና ወደ ስራ መመለሷ ተሰማ፡፡
ሀብል ቴሌስኮፕ ስራ ያቆመችው በፈረንጆቹ ከሰኔ 13 ጀምሮ መሆኑን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡
ካለፈው ሳምንት ወዲህ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌስኮፗ ላይ መጠነ ሰፊ የጥገና ስራ ተደርጎ የናሳ የጠፈር ተመራማሪዎች መረጃ መሰብሰብ እንደቻሉ ነው የተነገረው፡፡
እንደዚህ አይነት ትልቅ ብልሽት በዚህ ትልቅ ስም ባለው ተቋም ላይ ለዓመታት አጋጥሞ እንደማያውቅም ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡
ሀብል ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ስለ ጠፈር አስደናቂ እይታን ስታቀብለን የነበረች ምልክታችን ናት ሲሉ ገልፀዋታል የናሳ ሃላፊው ቢል ኔልሰን፡፡
ቴሌስኮፗ ወደ ጠፈር የመጠቀችው በፈረንጆቹ በ1990 ሲሆን ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የጠፈር ዕይታዊ ምስሎችንም እንዳቀበለች እና በመረጃዎቹ ወደ 18ሺህ ያህል የጥናት ወረቀቶች ለህትመት መብቃታቸው ነው በመረጃው የተጠቆመው፡፡ ምንጭ÷ ቢቢሲ