አዲስ አበባ፣ ጥር 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች ከዚህ ቀደም የፈረሙትን የሦስትዮሽ ስምምነት ለማስፈጸም ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋገጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ጋር በአስመራ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ መሪዎች መካከል በተካሄደው ውይይት፣ መስከረም ወር 2011 ዓ.ም የፈረሙትን የሦስትዮሽ ስምምነት ለማስፈጸም ያላቸውን ቁርጠኝነት ዳግም ማረጋገጣቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የስምምነቱን አፈጻጸም ከመገምገም ባለፈም ለ2012 እና ቀጣይ ዓመታት የጋራ የሽብር ስጋቶችን ለመቀልበስ፣ የሕገ-ወጥ የሰዎች፣ የመሣሪያ እንዲሁም የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ለመግታት የሚሆን የትግበራ ዕቅድ አውጥተዋል።
I held fruitful discussions with President Isaias Afwerki and Mohammed Abdullahi. We reaffirmed the 2018 Tripartite Agreement. We have developed a common understanding on consolidating peace, stability and security in our region as we also work on our socio-economic development. pic.twitter.com/HyqnNnrJil
— Abiy Ahmed Ali 🇪🇹 (@AbiyAhmedAli) January 27, 2020
በተጨማሪም፣ ሦስቱ መሪዎች ሀገራቱ ያሏቸውን የሰው እና የተፈጥሮ ሀብቶች በጥቅም ላይ በማዋል፣ የጋራ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ተስማምተዋል።
ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ የሶስትዮሽ ትስስራቸውን የሚያጎለብት የትብብር ስምምነት በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም በኤርትራ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዲላሂ ተፈራርመውታል።
የሶስትዮሽ የትብብር ስምምነቱ ሶስቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች በትብብር እንዲሰሩ የሚያስችል መሆኑም በወቅቱ ተገልጿል።