Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካሪዎች በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሃፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪዎች በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሃፊ አምባሳደር ቲቦር ናዥ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸው በኢትዮጵያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ላይ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል።

የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታውን መሰረት አድርጎ ሚኒስቴሩ ያከናወናቸው እና ወደፊት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸው ዋና ዋና የለውጥ ስራዎች ላይም ተወያይተዋል።

የመምህራንና አመራር አቅምን ከማሳደግ አንጻር የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ የሁለቱ ሃገራት ዩኒቨርሲቲዎች በትብብር በሚሰሩባቸው መስኮች፣ በዩኒቨርሲቲዎች ሰላምና ጸጥታን ከማስፈን አንጻር እንዲሁም ተመራቂ ተማሪዎችን ወደስራ ለማስገባት በትብብር ሊሰሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይም ምክክር አድርገዋል።

አምባሳደር ቲቦር ናዥ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፋዊ ለመሆን ለሚያደርጉት ጥረት እገዛ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው፥ በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ ድጋፍና ትብብሮች የሚደረጉበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተለይም ከግል የስራ ፈጣሪዎች ጋር ለማስተሳሰር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልጸዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትስስር ፈጥረው ቢሰሩ ተመራቂዎችን ወደስራ ማሰማራት እንደሚችሉ ጠቅሰው፥ በዚህ ዘርፍ በአሜሪካ መንግስት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

አምባሳደር ማይክል ራይነር በበኩላቸው አሜሪካ በኢትዮጵያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎችን ስትደግፍ መቆየቷን ጠቅሰው ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው አንስተዋል።

በውይይቱ ከአሜሪካ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተወካዮች፣ የአዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ሐረማያ፣ ጎንደር፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን እና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች መሳተፋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version