Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የውጪም ሆነ የውስጥ ጠላቶችን ጫና ተቋቁሞ መወጣት የሚቻለው በአንድነት ሲቆም ነው – የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሰራተኞች

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጪም ሆነ የውስጥ ጠላቶችን ጫና ተቋቁሞ መወጣት የሚቻለው በአንድነት ሲቆም መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሰራተኞች ገለጹ።

በቅርቡ በፀጥታው ምክር ቤት በቀረበው የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ የሦስትዮሽ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ በምክር ቤቱ አቋም መያዙ ይታወቃል።

ይህን ውሳኔ ተከትሎም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሠራተኞች እንዳሉት፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ የግብጽና የሱዳንን ኢ-ፍትሀዊ አካሄድ ከማሳየት ባለፈ ለስራችን ተጨማሪ ብርታት ሰጥቶናል።

የአፍሪካ ሀገራት ለችግሮቻቸው አፍሪካዊ መፍትሄን ማስቀደም እንዳለባቸውም ትምህርት የሰጠ ነው ያሉ ሲሆን፥ መድረኩ የግብጽ እና የሱዳን አካሄድ ፍትሃዊነት የጎደለው ስለመሆኑ ለዓለም ያሳየ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ከግድቡ ሠራተኞች መካከል አቶ ሃይሉ ካሳዬ እንዳሉት፥ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች እስከ ህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ለግድቡ ስኬት ሌት ተቀን እየሠሩ ነው።

“የጸጥታው ምክር ቤቱ የወሰደው አቋም ለፕሮጀክቱ ሠራተኞች ተጨማሪ ሞራል ሆኗል” ያሉት አቶ ሃይሉ፥ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ጠንክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

አቶ አበበ ተሻገር የተባሉ ሌላው የግድቡ ሠራተኛ በበኩላቸው፥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ያለመብራት በጨለማ እየኖሩ ግብጽ እና ሱዳን እውነታውን የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ህዝባቸው እንዲያውቅ ፈጽሞ እንደማይፈልጉም ነው የገለጹት።

“ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ መጠቀም በተመለከተ በየትኛውም መድረክ እውነታውን ይዛ ነው የምትሟገተው” ያሉት አቶ አበበ፥ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካዊያን በራሳቸው እንደሚፈቱ ያስተማረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ግድቡን ለፍጻሜ ከመብቃት ወደ ኋላ የሚመልስ ነገር እንደማይኖር የተረጋገጠበት መሆኑን ገልጸው፥ “በሰራተኛው ላይ የተፈጠረው መበረታታት እስከ መስዋዕትነት ለመክፈል ያነሳሳ ነው” ብለዋል።

“መጀመሪያም የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መሄድ እንደሌለበት ሁሉም የሚረዳው ሃቅ ነው” ያሉት ደግሞ ኮሎኔል ታምሬ ሙሉነህ የተባሉ የፕሮጀክቱ ሠራተኛ ናቸው።

ምክር ቤቱ ጉዳዮን በአፍሪካ ህብረት ለውይይት እንዲቀርብ መወሰኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፥ “በጸጥታው ምክር ቤት የተወሰደው አቋም ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም ለችግሮቻው በራሳቸው መፍትሄ መፈለግ እንዳለባቸው ትምህርት የሰጠ ነው” ብለዋል።

በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ የሃይል ማመንጫ ግድብ በመገንባት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንዳልሆነች የገለጹት ኮሎኔል ታምሬ፥ ሃብቷን በማልማት ለመጠቀም እያደረገችው ያለው ጥረት ወትሮም በተለየ ሁኔታ መታየት እንደሌለበት አመላክተዋል።

ኮሎኔል ታምሬ ጨምረውም፥ የውጪም ሆነ የውስጥ ጠላቶችን ጫና ተቋቁሞ መወጣት የሚቻለው በአንድነት ሲቆም መሆኑንም ገልጸዋል።

አቶ መሃሪ አንተነህ የተባሉ ሠራተኛ በበኩላቸው የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ትውልዱ የራሱን አኩሪ ታሪክ የሚያስቀምጥበት መሆኑን ተናግረዋል።

የግብጽ እና ሌሎች ሃገራት ስጋትም ኢትዮጵያ ወደ ልማት የምታደርገው ይሄው ጉዞ እንደሆነ አቶ መሃሪ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version