የሀገር ውስጥ ዜና

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና ኢ/ር አይሻ መሃመድ የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን አጸዱ

By Alemayehu Geremew

July 10, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂር አይሻ መሃመድ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን አጸዱ።

“የከተማችን የፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች የውሃ መውረጃ እንጂ የቆሻሻ መጣያ አይደሉም!” በሚል 2ኛው የፍሳሽ መውረጃ ቱቦዎች እና መስመሮች የፅዳት ዘመቻ ንቅናቄ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተካሂዷል ።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚንስትር ኢንጂር አይሻ መሃመድ ጋር በመሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ላፍቶ አካባቢ በሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ችግኝ በመትከል እና የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን አጽድተዋል።

ቆሻሻ የሚጥሉ እጆች ሳይሆን ቆሻሻ የሚያነሱ እጆች ይበረታታሉ ያሉት ወይዘሮ አዳነች ÷ ነዋሪዎች ቆሻሻን ባለመጣል ለከተማዋ ውበት እና ጽዳት የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ብለዋል።

በባለፉት ወራት የጽዳት ዘመቻ መርሃ ግብሮች ከ6 ሺህ ኪሎሜትር በላይ የውሃ መውረጃ ቱቦዎች የጸዱ መሆናቸውን የገለፁት ምክትል ከንቲባዋ÷ በዚህም ከ3 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች ተሳታፊዎች መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚንስትር ኢንጂር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው÷ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎችን በማስተባበር አካባቢን በማጽዳት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ለሌሎች ከተሞችም አርዓያ የሚሆን በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዛሬው ዕለትም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ የጸጥታ አካላት፣የጽዳት ሰራተኞች እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የጽዳት ዘመቻ መርሃ ግብር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተካሂዷል ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!