አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ላለፉት 30 አመታት ጥልቁን የህዋ ክፍል ስትቃኝ የሰው ልጅ በዘርፉ የሚያካሂደውን ምርምር በእጅጉ ስታግዝ ኖራለች።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1990 ሚያዝያ ወር ወደ ህዋ የተወነጨፈችው መንኮራኩር የተሸከመቻትና ለጠፈር ምርምር አጋዥ የሆነችው ሀብል ቴሌስኮፕ ወደ ምድር ምህዋር በስኬት ለመግባት የፈጀባት ስምንት ደቂቃ ብቻ ነበር።
ምንም እንኳ መንኮራኩር በስኬት ማምጠቅ በራሱ ትልቅ ውጤት ቢሆንም የሃብል ቴሌስኮፕ በስኬት ተልዕኮዋን እንድትጀምር ማድረግ ለህዋ ምርምር ሳይንስ ትልቅ እመርታ ሆኗል።
የዘርፉ ተመራማሪዎች የሃብል ቴሌስኮፕ ስኬት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ቴሌስኮፗ የምትልካቸው የጥልቁ ህዋ ምስሎችና መረጃዎች የህዋ ምርምር ሳይንስ መፅሃፍትን ዳግም ለመፃፍ ማስቻሉን ያነሳሉ።
ሃብል ቴሌስኮፕ በብዙ መቶ ቢሊየኖች የሚቆጠሩ ኮኮቦችን አፈጣጠር የሚያሳዩ ምስሎችን፣ የተለያዩ ፕላኔቶችን በርባኖስ (ጥልቅ የጨለማ ክፍል) ምስሎችንና መረጃዎችን፣ የጥንታዊ ጋላክሲዎችን ምስሎች በመላክ ቴሌስኮፗ በዓለም የህዋ ሳይንስ ምርምር ዘርፍ ላይ አሻራዋ ትልቅ ነው።
ከሶስት አስርት አመታት በላይ ጥልቁን ህዋ ስትቃኝ የቆየችው ሃብል ቴሌስኮፕ አሁን አገልግሎቷን ሳትጨርስ አልቀረችም ተብሏል።
ቴሌስኮፗ ካሏት መሰረታዊ ቁሳቁሶች አንዱ ከባድ ብልሽት እንዳጋጠመው የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) ይፋ አድርጓል።
የናሳ ባለሙያዎች ጥገናውን ለማድረግ ቢሞክሩም ጥረታቸው እስካሁን ውጤት እንዳላመጣም ነው የተነገረው።
በእርግጥ ሃብል ቴሌስኮፕ በተለያየ ጊዜ ብልሽት አጋጥሟት አምስት ጊዜ ጥገና ተደርጎላታል።
አሁን አጋጠማት የተባለውን ብልሽት ለመጠገንና ሃብልን ወደ ቀደመ ተግባሯ ለመመለስ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎችን ወደ ቴሌስኮፗ በአካል መላክ እንደሚያስፈልግና ይህም አመታትን የሚፈጅ ዝግጅት ይጠይቃል ብሏል ናሳ።
በእርግጥ የዘመናዊ ህዋ ሳይንስ ምርምር ባለውለታዋ ሃብል ቴሌስኮፕ ስራ ማቆም ለዘርፉ ያለው አንድምታ ከፍተኛ ቢሆንም “ይህ እንደሚመጣ ቀድመን አውቀን ዝግጅት ላይ ነበርንም” ነው ያለው።
ለዚህ እንዲረዳም ሃብልን የሚተካት ጄምስ ዌብ የተባለ ቴሌስኮፕ ተዘጋጅቶ እንደነበርም ናሳ አስታውቋል፡፡
ቴሌስኮፑ በ100 እጥፍ የተሻለ ጉልበት እንዳለውና የሚልካቸውን ምስሎች በተሻለ ጥራት እንደሚያቀርብም ነው ተቋሙ ያስታወቀው።
በ10 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደተሰራ የተነገረለት ጄምስ ዌብ ቴሌስኮፕ የሚመጥቅበት ጊዜ ለአመታት እየተራዘመ ቢመጣም ዘንድሮ ተሳክቶለት ሃብልን ሊተካ እንደሚችልም የሲ ኤን ኤን ዘገባ አመላክቷል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!