አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ነገር እንከፍላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይአሕመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላት ለሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ኢትዮጵያ በሰላምና በትብብር መልማት ትፈልጋለች ብለዋል፡፡
ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ነገር እንከፍላለን ፣ በግልጽ የሚታይ አደጋ እስካልመጣ ድረስም ከማንም ኃይል ጋር ውጊያና ግጭት አንፈልግም ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል የሚጓተተውን የመንገድ ግንባታ ለመፍታት ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመንገድ ግንባታ ሂደትን በመከታተል ረገድ ሰፊ ክፍተት መኖሩን አንስተዋል፡፡
ለመንገድ ግንባታ በጀት ከተያዘ በኋላ ለካሳ ክፍያ በርካታ ገንዘብ ይባክናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካሳ ክፍያም ፕሮጀክትን ሳያስተጓጉል መፈጸም አለበት ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የቱሪዝም ሃብቱን የማስተዋወቅ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚያስፈልግ በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡
የሲሚንቶ እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው÷ የሲሚንቶ እጥረት ከፍተኛ መሆኑ በግንባታው ዘርፍ ጫና መፍጠሩን አውስተዋል፡፡
በሌላ በኩልም ሃገራዊ ፕሮጀክቶች የሚወስዱት ከፍተኛ መጠን ያለው ሲሚንቶ ለእጥረቱ በመንስኤነት ጠቅሰዋል፡፡
ከምርጫ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ ምርጫው እንደ ሃገር የተማርንበትና ህዝቡም የተማረበት ነበር ብለዋል፡፡
በምርጫው የኢትዮጵያ አሸናፊነት የታየበት ነው፤በምርጫው የሚመለከታቸው ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ያደረጉት ጥረትና የሰሩት ስራ የሚደነቅና ሊበረታታ የሚገባው ነውም ብለዋል፡፡
በዲፕሎማሲ ተቋምን ማደስ ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያንስ 30 ኤምባሲዎችን እንደሚቀነሱ አስታውቀዋል፡፡
በመላው ዓለም ከአምባሳደሮች የሚልቁ ኢትዮጵያውያን አሉ ትልልቅ ስራዎችን ይሰራሉ እነሱን ወደ ስራ ማስገባት ያስፈልጋ ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ተሿሚ ሚኒስትሮች ሾፌር አይቀጠርላቸውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸው እንዲያሽከረክሩ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመቀነስ ኢትዮጵያን መተባበር እንደሚያስፈልግ ገልፀው ከዚህ በተጨማሪ የግል ሴክተሩ እንዲሳተፍበት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ወደተገነቡ ማእከላት ማስገባት ብቻ ሳይሆን ማቆየትም ይገባል፤ ሱስ፣ወላጅ ማጣት፣የተለያዩ ባህሪያት ልምምድ ስላለባቸው በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!