አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት “ማረፊያ” የተሠኘ የሬዲዮ መዝናኛ ፕሮግራም በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል።
ዘውትር ቅዳሜ ከ5:00-900 ሰዓት በፋና ኤፍ ኤም 98.1 ለአድማጭ የሚደርሠውን ፕሮግራም የኮርፖሬቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አድማሡ ዳምጠው፣የይዘት ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ሠጠኝ እንግዳውና ተባባሪ ፕሮፌሠር ነብዩ ባዬ በጋራ አስጀምረዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሬዲዮ፣በቴሌቪዥንና በዲጂታል ሚዲያዎች ከሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ተነስቶ ለሕዝብ ጥቅም አበክሮ እንደሚሠራ አቶ አድማሱ ተናግረዋል።
ፋና መልካም የሥራ ባሕልን ያዳበሩ፣ትጉሕ ሠራተኞች የነበሩትና ያሉት ተቋም እንደሆነ የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው÷ ከአድማጭ ተመልካች ፍላጎት አንፃር በሚጎድሉን ላይ እየሠራን የተሟላ፣ተወዳጅና ተመራጭ የሚዲያ ተቋም ለመሆን እየታተርን ነው ብለዋል።
የይዘት ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ሠጠኝ እንግዳው በበኩላቸው÷ ተቋሙ በቅርቡ አዲስ መዋቅርና አደረጃጀት ተግባራዊ ማድረጉን አውስተው÷ በሁሉም ሚዲየሞች የዜናና ፕሮግራሞች የአቀራረብና የይዘት ማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ለዓመታት ከፋና ጋር በአድማጭነት፣በተመልካችነትና በተሳታፊነት የካበተ ልምድ እንዳላቸው የመሠከሩት ተባባሪ ፕሮፌሠር ነብዩ ባዬ የአሁን ጊዜ የሬዲዮ መዝናኛ ፕሮግራሞች የጠለቀ የዝግጅትና የጥናት ሥራ እንደሚጎድላቸው ተችተው፤ፋና በዚህ ረገድ የተሻለ መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዛሬ ከአስጀመረው”ማረፊያ”የመዝናኛ ፕሮግራም ሌላ እሁድ ምሽት “ካሉበት ይሞክሩ”የጥያቄና መልስና ፕሮግራም እንዲሁም ከሰኞ ምሽት ጀምሮ “አመፀኛው ክልስ” የመፅሐፍ ትረካ ይጀምራል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!