አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ጠየቀ።
ዓለም አቀፉ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) የአንበጣ መንጋው በምግብ ዋስትና ላይ የደቀነውን ስጋት ለመከላከል ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቋል።
በአንበጣ መንጋው አሁን ላይ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ መጠቃታቸውንም ድርጅቱ ገልጿል።
የአንበጣ መንጋው የሚዛመትበት መጠን ከፍ ያለ መሆኑ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አዳጋች እንዳደረገውም ነው ያስታወቀው።
በዚሁ ከቀጠለም እስከ ሰኔ ወር ድረስ የአንበጣው ቁጥር 500 እጥፍ ሊያድግ እንደሚችል ስጋት መኖሩም ነው የተነገረው።
አሁን ላይ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ብቸኛው አማራጭ በአውሮፕላን ፀረ ተባይ መድሃኒቶችን መርጨት መሆኑም ተጠቀሟል።
የአንበጣ መንጋው ከምስራቅ አፍሪካ በተጨማሪ በህንድ፣ ኢራን እና ፓኪስታን መከሰቱም ተገልጿል።
አንበጣ በአንድ ቀን ውስጥ እስከ 150 ኪሎ ሜትር መጓዝ ከመቻሉም ባለፈ በየቀኑ የራሱን ክብደት የሚያህል ሊመገብ እንደሚችል ይነገራል።
ምንጭ፦ ቢ.ቢ.ሲ