Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአነስተኛ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችና ሞተሮች መፈተሻ ማዕከል ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የአነስተኛ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችና ሞተሮች መፈተሻ ማዕከል ተከፈተ።

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ካባ ዑርጌሳ፥ በሃገራችን መሰረታዊ የልማት ጥያቄና ቁልፍ ችግሮችን ለመመለስ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን እንደ መነሻ በመጠቀም የግብርና ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ማነቆዎችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰደ ነው ብለዋል።

አያይዘውም የአፈጻጸም ክፍተቶችን ለመፍታትና በቴክኖሎጂ አቅርቦትና ተከላ የሚስተዋሉ ቁልፍ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የመስኖ ልማቱ በተሻለ ጥራት እንዲከናወን ለማስቻል ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ለመስራት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

ማዕከሉ ለመስኖ ውሃ መሳቢያ ሞተሮችና ፓምፖች ጥገና የሚወጣውን አላስፈላጊ ወጪ በመቀነስ ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥራቱን የጠበቀ የመስኖ ፓምፕ ለማቅረብና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት መቋቋሙን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ወደፊት የቴክኖሎጂ ጥራትን ለማጎልበት ለተጀመረው እንቅስቃሴ ትልቅ መሰረት ነው ማለታቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version