አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጂቡቲ የንግድ ልዑካን ቡድን በዱከም ከተማ የሚገኘውን ኢንዱስትሪ ዞን እና የሞጆ ደረቅ ወደብን ጎብኝቷል።
በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው በጅቡቲ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የተመራ የንግድ ልዑካን ቡድን በዛሬው እለት ኢስተርን ኢንዱስትሩ ዞን ጉብኝት አድርጓል።
በጉብኝቱም ልዑካን ቡድኑ በኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኙትን የሳንሼንግ ፋርማሲዩቲካል እና ዩዋን ሴራሚክስ ፋብሪካዎችን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
በተጨማሪም የሞጆ ደረቅ ወደብን የስራ እንቅስቃሴም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የጅቡቲው ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሱፍ ሙሳ፥ ኢትዮጵያ የባህር በር ባይኖራትም በደረቅ ወደብ የምታከናውነው የስራ እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።
የሞጆ ደረቅ ወደብ የባህር መውጫ በር ለሌላቸው የጎረቤት ሀገራት እንደ ደረቅ ወደብም ለማገልገል ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የጅቡቲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመመልከት የሚሰሩበት ሁኔታ መኖሩንም አክለዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርእሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አሚን ጁንዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጅቡቲ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራሉ ብለዋል።
የጅቡቲ ባለሃብቶች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በመለየት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ መግለፃቸውንም የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።