አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሊቢያ ጎረቤት ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትሪፖሊ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በአልጀሪያ እየመከሩ ነው።
የግብፅ፣ ቻድ፣ ኒጀር፣ አልጀሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ማሊ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትሪፖሊ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን በሚቻልበት አግባብ ላይ በአልጀርስ መምከር ጀምረዋል።
የአልጀርሱ ውይይት ሊቢያ ጠንካራ ተቋማትን እንድትገነባ እና ወደ መረጋጋት እንድትመለስ የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦችን ለማቅረብ ያለመ ነው ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ለሊቢያ ቀውስ እልባት ለመስጠት የጦር መሳሪያ እግድ እንዲጣል ግፊት እንደሚያደርጉም ነው የተነገረው።
በተያያዘ ዜና የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የሊቢያ ቀውስ በአካባቢው ሃገራት ሽብርተኝነት እንዲስፋፋ ያደርጋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ዋና ፀሃፊው በሊቢያ ያለው ቀውስ በሳህል ቀጠና እና በቻድ ሃይቅ አካባቢ ሃገራት ሽብርተኝነት እንዲስፋፋ ያደርጋል ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ዓለም አቀፍ እውቅና ባለው የፋይዝ አል ሳራጅ አስተዳደር እና በተቀናቃኛቸው ጄኔራል ከሊፋ ሃፍታር መካከል የተፈጠረው ግጭት ለሊቢያ የቀውስ ምንጭ ሆኗል።
ባሳለፍነው ሳምንት ሁለቱ ሃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ በሞስኮ ድርድር ጀምረው የነበረ ቢሆንም፥ ጄኔራል ከሊፋ ሃፍታር የተኩስ አቁም ስምምነቱን ሳይፈርሙ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።
ሃገራትም ተፋላሚ ሃይሎቹ ልዩነታቸውን በመፍታት ወደ ስምምነት እንዲመጡ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ምንጭ፦ አልጀዚራ