Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች ጋር እየተወያዩ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች ዙሪያ ከደቡብ ወሎ ዞን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በደሴ ከተማ እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ የፌደራልና የአማራ ክልል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ከ24 ወረዳዎች የተውጣጡ የቀበሌና የወረዳ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓሊ ሰይድ እንደገለጹት፥ ውይይቱ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና አጠቃቀም ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችና ጥንካሬዎችን መሠረት ያደረገ ነው።

በተለይም በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት የበጋ ወቅት ሥራዎች ውጤታማነት እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

የዘንድሮውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከማስጀመር ጋር ተያይዞ የተሻለ መግባባት ለመድረስ እንደሚረዳም አቶ ዓሊ ገልጸዋል።

በዞኑ በበጋ ወቅት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከ610 ሺህ በላይ ሕዝብ ከ1 ሺህ በሚበልጡ ተፋሰሶች ውስጥ ሥራውን ያከናውናል ብለዋል።

በሥራው ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይሸፈናል ያሉት ምክትል ኃላፊው፥ በዚህም የደን ሽፋኑን አሁን ካለበት 13 በመቶ ወደ 14 በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

Exit mobile version