ዓለምአቀፋዊ ዜና

ትራምፕ ነፍሰ ጡር ሴቶች ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉዞ የሚከለክል አሰራር ሊተገብሩ ነው

By Tibebu Kebede

January 24, 2020

አዲስ አበባ ፣ ጥር 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ነፍሰ ጡር ሴቶች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ አሰራር ተግባራዊ ሊያደርግ ነው።

አዲሱ አሰራር ነፍሰ ጡር ሴቶች በአሜሪካ ምድር ልጅ በመውለድ ልጆቻቸው የአሜሪካ ዜግነት እንዲያገኙ ለማስቻል የሚያደርጉትን ጥረት ለመከላከል ያለመ ነው።

አሰራሩም ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ከነጬ ቤተ መንግስት የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም ቢ1 እና ቢ2 የአጭር ጊዜ የጉብኝት ቪዛን ከሌሎች ሃገራት ወደ አሜሪካ ለሚጓዙ ነፍሰ ጡር ሴቶች አይሰጥም ነው የተባለው።

የቪዛ ክልከላው የሚመለከታቸው ነፍሰ ጡር ሆነው በአሜሪካ ምድር በመውለድ ልጆቻቸው የአሜሪካ ዜግነት እንዲያገኙ ለማድረግ በማሰብ ጉዞ የሚያደርጉ ናቸው ተብሏል።

ይሁን እንጅ አዲሱ አሰራር በአብዛኛው ከአውሮፓ የሆኑ የ39 ሃገራት ዜጎችን አይመለከትም ነው የተባለው።

አሰራሩ የማይመለከታቸው የአሜሪካ መንግስት ለሃገራቱ ዜጎች ያለምንም ቪዛ ለጉብኝት፣ ለግል ጉዳዮች፣ ቢዝነስ እና መሰል ጉዳዮች የ90 ቀናት የጉብኝት ፈቃድ የሰጣቸው ናቸው።

በየአመቱ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ ሃገራት ነፍሰ ጡር ሴቶች በአሜሪካ ምድር እንደሚወልዱ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ምንጭ፦ ሲ ኤን ኤን