ጤና

የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በከባድ ጭንቀት እንዲሚጠቁ ተገለፀ

By Tibebu Kebede

January 24, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥር 15 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ከፍተኛ ለሆነ የአካል ውጥረት እና ጭንቀት እንደሚጋለጡ ጥናት አመለከተ።

ጥናቱ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ቡድናቸውን በሚደግፉበት ወቅት በሚፈጠር ከባድ ውጥረት ለልብ በሽታ እንደሚጋለጡ አመላክቷል።

ብራዚል በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ በጀርመን 7 ለ 1 በተሸነፈችበት ወቅት የብራዚል ደጋፊዎች የነበራቸውን ስሜት የኦክስፎርድ ጥናት ተመልክቷል።

በ2014 በነበሩ ሶስት የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በፊት እና በኋላ 40 የሚሆኑ ደጋፊዎች የስሜት መቀያየር ሲፈጠር ሰውነታቸው የሚያመነጨው የሆርሞን መጠን ክትትል ተደርጎበታል።

በዚህም በተደረጉ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች የጭንቅት ወይም የውጥረት ደረጃቸው ከፍ ብሎ የታየ ሲሆን የብራዚል ደጋፊዎች በጀርመን በሰፊ የጎል ልዩነት ሲሸነፉ ሰውነታቸው በውጥረት ወቅት የሚለቀው የሆርሞን መጠን ከፍ ብሎ ታይቷል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ በደጋፊዎቹ ላይ የደም ግፊት እንዲጨምር እና ለልብ በሽታ እንዲጋለጡ ያደርጋልም ነው የተባለው።

ጨዋታው ፍርሃትን የሚፈጥር በመሆኑ በበርካታ ደጋፊዎች ላይ ለተፈጠረው የሀዘን ስሜት ምክንያት መሆኑን በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ትስስር የጥናት ማዕከል ተመራማሪ ዶክተር ማርታ ኔውሰን ተናግረዋል።

ሆኖም ደጋፊዎች ቀልድን በመፍጠር እና በመተቃቀፍ በወቅቱ ጭንቀታቸውን እና ውጥረታቸውን ለመቀነስ ሲሞክሩ ተስተውለዋል።

ዶክተር ማርታ ስቴዲየሞች ከጨዋታ በኋላ መብራቶችን በመቀነስ ለደጋፊዎች ሙዚቃ እንዲጋብዙም መክረዋል፡፡

ክለቦችም በስቴዲየም ለማይጠፉና በጨዋታዎች ወቅት ለጭንቀት ለሚጋለጡ ደጋፊዎቻቸው የልብ እና ሌሎች የጤና ምርመራዎችን እንዲያገኙ ሊሰሩ እንደሚገባም ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

ለክለባቸው እና ለሀገራቸው የእግር ኳስ ድጋፍ ቅርብ በሆኑ ሴቶችና ወንዶች የሚከሰተው ችግር ልዩነት እንደሌለውም ነው የተነገረው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ